የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀገር ባለውለታ ናት- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀገር ባለውለታ ናት- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- መጋቢት 8/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

ከንቲባዋ በውይይታቸው የመደመር መንግስት ለቤተክርስቲያኗ ያለውን ጥልቅ ክብርና እውቅና በዝርዝር ገልጸዋል።

ከንቲባዋ የመድረኩ ዋና ዓላማ በመንግስትና በቤተክርስቲያኗ መካከል ያለውን ግንኙነት ግልጽ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ያለንበት ዘመን ያልተባለ የሚባልበትና የሀሰት ትርክቶች የሚነዙበት በመሆኑ፣ ይህን ብዥታ በማጥራት የጋራ ተግባቦት ላይ መድረስ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች ቤተክርስቲያኗ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መገንባት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ ለያዘችው ቅርጽ፣ ለሉዓላዊነቷና ለሰላሟ ቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ሚና መጫወቷንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንስተዋል።

ቤተክርስቲያኗ ሥነ-ምግባር ያለው ትውልድ በመገንባትና የሀገር የወል ትርክቶች እንዲሰርጹ በማድረግ ረገድም ትልቅ ባለውለታ ናት ሲሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥንታዊነቷ እንድትታወቅ ያደረጉ ቅርሶችን በመጠበቅና ለቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለሀገር ኩራት ሆናለች ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአደስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ሥራ ቤተክርስቲያኗ ላሳየችው አርአያነት ያለው ትብብርም ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም አሁንም ቤተክርስቲያኗ የምታነሳቸው ጥያቄዎች እንዳሉ በመግለፅ፣ እነዚህን ጥያቄዎች በፍትሃዊነትና በቅደም ተከተል በጊዜ ሂደት ለመመለስ መንግስት ቁርጠኛ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review