AMN መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ ከአፍሪካ ህብረት የቅድመ-ምርጫ ግምገማ የመጣን ልዑክ በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮችን የያዘውን ይህንን ልዑክ የሚመሩት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፍሪ ኦኒያማ ናቸው።
በውይይቱ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ አፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ አስቀድሞ የቅድመ-ምርጫ ግምገማ ልዑክ በመላኩ አመስግነዋል። ሚኒስትሩ ልዑኩ ስራውን በብቃት ማከናወን እንዲችል የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።
ጄፍሪ ኦኒያማ በበኩላቸው፣ የቅድመ-ምርጫ ግምገማ ልዑኩ ዋና ዓላማ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ስለሚመጣው ምርጫ ዝግጅት ቀጥተኛ መረጃዎችን ማሰባሰብ እንደሆነ መግለጻቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡