AMN መጋቢት 8/2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ መሰረተ ልማት ላደረጋቸው ሪፎርሞች ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል።
ብሔራዊ ባንኩ ሽልማቱን ያገኘው ተቀማጭነቱን በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ካደረገው ሴንትራል ባንኪንግ ፐብሊኬሽን (Central Banking publication) ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።
የፋይናንስ ህትመት እና መረጃ ድርጅቱ ትኩረቱን የሚያደርገው በማዕከላዊ ባንክ፣ በፋይናንስ ገበያዎች እና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ሲሆን የተለያዩ የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ሪፖርቶችን ያወጣል።
ባንኩ ሽልማቱን ያገኘበት ዘርፍ “የክፍያና የፋይናንስ ገበያ ስርዓት ማሻሻያ –ጅምላ ንግድ” የሚል ነው።
ሴንትራል ባንኪንግ ፐብሊኬሽን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሀገሪቷ ቁልፍ የፋይናንስ መሰረተ ልማት ላይ ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ማድረጉን አመልክቷል።
የፋይናንስ መሰረተ ልማት ማሻሻያ ስራው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተተገበረ የሚገኘው የአጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል እንደሆነም ገልጿል።
ሞኒተሪ ፖሊሲው ወደ ወለድ ምጣኔ እና ዋጋ ንረት ተኮር ስርዓት መሸጋገሩንና የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ በገበያ መመራት መጀመሩ ከሪፎርሞቹ መካከል እንደሚጠቀሱም ነው ያስታወቀው።
ባንኩ የሪፎርሙ አካል የሆኑ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል።
ባንኩ የመንግስት ግምጃ ሰነዶች እና የፋይናንስ ሀብቶች ሽያጭ እና ግዢ (Open Market Operations) ለማጠናከር፣ የገንዘብ አስተዳደርን (Treasury Management) ለማሳለጥ እና የካፒታል ገበያን ለማልማት የሚያስችሉ እንደ ልዩ የፋይናንስ መሰረተ ልማት ተቋማት (Central Securities Depository) ማቋቋምን ያሉ ቁልፍ ስርዓቶችን አስተዋውቋል።
እርምጃዎቹ የገንዘብ ፖሊሲ ለማሻሻል እና አጠቃላይ የገበያ ቅልጥፍናን ለማሳደግ ያለሙ ናቸው።
ማሻሻያዎቹ የዲጂታል ክፍያን ለማስፋፋት እና ሁሉንም ያካተተ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያ ለፋይናንስ ዘመናዊነት እና ዲጂታላይዜሽን ከምታደርገው ሰፊ ጥረት ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያያት ሽልማቱ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳችን የታቀዱትን የገበያ መሠረተ ልማት፣ የገበያ ሥርዓት እና የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በቁርጠኝነት እንድንቀጥል ብርታት ይሆነናል ብለዋል።
እውቅናው አገሪቱ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለበለጠ ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ ያላትን ቁርጠኝነት ለማጠናከር እንደሚያስችል ተመላክቷል።
ሴንትራል ባንኪንግ ፐብሊኬሽን (Central Banking publication) ዓለም አቀፍ ድርጅት እ.አ.አ በ1990 የተቋቋመ ሲሆን ከእ.አ.አ 2011 ሽልማቶችን በተለያዩ ዘርፎች እየሰጠ ይገኛል።
ድርጅቱ በዓለም ደረጃ ለሚገኙ ማዕከላዊ ባንኮች የልህቀት ስራ፣ ኢኖቬሽን እና ምርጥ ተሞክሮዎች እውቅና ይሰጣል።