AMN- መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ዙር የመልስ ጨዋታቸውን ያደረጉት አርሰናል ፣ ሪያል ማድሪድ እና ፓሪሰን ዠርማ በድምር ውጤት በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል።
በሜዳው ኢትሃድ ሪያል ማድሪድን የገጠመው ማንችስተር ሲቲ 2ለ1 ተሸንፏል።
ማድሪድ ቪኒሺየስ ጁኒዮር በፍፁም ቅጣት ምት መምራት ችሎ ነበር። ኳስ በእጅ በመንካት ፍፁም ቅጣት ምቱ እንዲሰጥ ምክንያት የሆነው በርናርዶ ሲልቫ በቀጥታ ቀይ ካርድ ወጥቷል።
የሲቲን የአቻነት ግብ ኧርሊንግ ሃላንድ አስቆጥሯል። ኖርዌያዊው አጥቂ በቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን ግቦች 57 አድርሷል። ይህም የምንግዜም ሰባተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንዲሆን አስችሎታል።
ማድሪድ በቪኒሽየስ ሌላ ግብ አግኝቶ ጨዋታውን 2ለ1 ማሸነፍ ችሏል። የመጀመሪያውን ጨዋታ 3ለ0 አሸንፎ የነበረው ማድሪድ በድምር ውጤት 5ለ1 በመርታት ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል።
ማድሪድ በቀጣይ የባየርን ሙኒክ እና አታላንታን አሸናፊ ይገጥማል። በሜዳው ኤምሬትስ ከባየር ሊቨርኩሰን ጋር የተጫወተው አርሰናል 2ለ0 አሸንፏል።
ኤብሪቼ ኤዜ እና ዴክላን ራይስ ያስቆጠሯቸው ግቦች መድፈኞቹን ባለድል አድርገዋል። በጨዋታው አስደናቂ ግብ ያስቆጠረው ኤብሪቼ ኤዜ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቦለታል።

የመጀመሪያውን ጨዋታ 1ለ1 ተለያይቶ የነበረው የሰሜን ለንደኑ ክለብ በድምር ውጤት 3ለ1 በማሸነፍ የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆኗል። ለሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዓመት ሩብ ፍፃሜ የገባው አርሰናል በቀጣይ ከፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ይጫወታል።
በሌላ ጨዋታ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ በፓሪሰን ዠርማ 3ለ0 ተሸንፏል። ክቪቻ ክቫራስኬሊያ ፣ ብራድሊ ባርኮላ እና ሴኒ ማዩሉ የፈረንሳዩ ክለብ የማሸነፊያ ግቦች ያስገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
የባለፈው ውድድር ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ፒ ኤስ ጂ በአጠቃላይ ውጤት 8ለ2 በማሸነፍ ነው ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፈው። በቀጣይም የሊቨርፑል እና ጋላታሳራይ አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ