የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ100 ሺህ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አከናወነ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ100 ሺህ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አከናወነ

AMN – መጋቢት 9/2018 ዓ.ም

የዘንድሮውን የዒድ አል-ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

ዛሬ ማለዳ የተጀመረው ይህ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው ወገኖች ቅድሚያ በመስጠት የተከናወነ ነው።

ከንቲባዋ እንደገለጹት፣ ይህ ተግባር ቀደም ሲል በሌሎች በዓላት ላይ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ተደራሽ መሆን ችሏል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በረመዳን ወር ሙሉ በከተማዋ በሚገኙ 28 የምገባ ማዕከላት 27 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ያለ ምንም ችግር ወሩን እንዲያሳልፉ የአፍጥር ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸው እንደነበር አስታውቀዋል።

የዚህ መርሐ ግብር ዋና ዓላማ ጊዜያዊ ችግርን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ያለውን ክብር ለመግለጽ እንዲሁም የወንድማማችነትና የጋራ መደጋገፍ እሴትን ለማጎልበት መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

በከተማዋ በሚከናወኑ እነዚህ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በማስተባበርና አቅመ ደካሞችን በጉልበታቸው በመርዳት ለተሳተፉ ወጣቶች፣ እንዲሁም ካላቸው ቆርሰው ለሰጡ ባለሀብቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ከንቲባዋ በተጠቃሚዎች ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይም በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል ለተደረገው የማዕድ ማጋራት ድጋፍ ላበረከቱት ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ እና ለዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ ልዩ ዕውቅና ሰጥተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመጨረሻም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ የደስታ፣ የሰላምና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን “ዒድ ሙባረክ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review