የዒድ አል-ፈጥር በዓል ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል – የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

You are currently viewing የዒድ አል-ፈጥር በዓል ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል – የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

AMN – 9/2018 ዓ.ም.

የዒድ አል-ፈጥር በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ 1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

መግለጫውን የሰጡት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ ሸሪፍ፣የዘንድሮውን በዓል ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዘንድሮውን የረመዳን ወርና የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ለየት የሚያደርገው፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በነቂስ ወጥቶ ይመሩኛል ያላቸውን መሪዎች በነጻነት በመምረጥ ለተቋማዊ ግንባታ ሥራው ጠንካራ መሠረት የጣለበት ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው፣ የእስልምናን ወንድማማችነት ለማጽናትና አንድነትን ለመገንባት ያደረጋችሁት ጥረት ለሁላችንም ኩራት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሺሀቡዲን ሼኑራ በዘንድሮው የረመዳን ወር በየመስጂዱና በየአካባቢው የረመዳን ወር እውነተኛ ትርጉም በተግባር የታየበት የየቀኑ የኢፍጣር ሥራ እና በየአካባቢው የተካሔደው የማዕድ ማጋራት ለብዙ አባወራዎችና እማወራዎች ትልቅ እፎይታን ሰጥተዋል ብለዋል፡፡

በበዓሉም ቀንም ይህ ተግባር እንዲቀጥል ዘካተል-ፊጥርን በየጊዜው ለሚስኪኖች በማድረስ፣የተቸገሩትን በመርዳት በደስታ በዓሉን እንዲያሳልፉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት::

የዘንድሮው የዒድ አል-ፈጥር በዓል አከባበር ሥርዓቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በበዓሉ ዐቢይ ኮሚቴ የሚቀርበውን የጥንቃቄ መልዕክትና መመሪያዎች መላው የከተማዋ ሙስሊም ማኅበረሰብ በትኩረት አድምጦ ሊተገብር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይም የአዲስ አበባን ውበትና ንጽህና መጠበቅ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት በመሆኑ፣ ለሰላት ስትወጡ ካርቶኖችንና ጋዜጣዎችን ከመጠቀም በመቆጠብ መስገጃ (ሰጃዳ) ብቻ ይዛችሁ በመውጣት የበዓሉን ድምቀትና የከተማችንን ጽዳት መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።

የዐብይ ኮሚቴው ሰብሳቢና የሥራ አስፈጻሚ አባል ኡዝታዝ ሼህ ሁሴን ሰይድ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ወደ በዓሉ ሲሄድ የተከለከሉ ነገሮችን ባለመያዝና ለጸጥታ አካላት ታዛዥ በመሆን ሰላሙን ሊያስጠብቅ ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።

በሔለን ጀንበሬና መሐመድ ፈንታው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review