AMN-9/2018ዓ.ም
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ1447ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልን በማስመልከት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ። ምክር ቤቱ በረመዳን ወር የታየው የመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን የማሰብ በጎ እሴት በበዓል ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብድልከሪም ሼህ በድረዲን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ህዝበ ሙስሊሙ የዘንድሮውን የኢድ አልፈጥር በዓል ሲያከብር የታመሙትን በመጠየቅና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ላይ እንዳመለከቱት፣ በረመዳን ወር የታየው መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ መተባበር እና መደጋገፍ በበዓሉ ዕለትም ሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ስር ሊሰድ የሚገባ ተግባር ነው። ህዝበ ሙስሊሙ በጾሙ ወቅት ካለው ላይ በማካፈልና በመረዳዳት በረከት ሲያገኝ እንደቆየ ሁሉ፣ ይህ የመጠያየቅ እሴት በቋሚነት ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን በጋራ ማገዝ የሃይማኖታዊና የወንድማማችነት ግዴታ መሆኑን ሼህ አብድልከሪም ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ የእምነቱ ተከታዮች ዘካተል ፊጥርን በወቅቱ በማውጣት፣ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርስ በማድረግ በዓሉን በጋራና በደስታ ማክበር እንዳለባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በመሀመድኑር ዓሊ