AMN-መጋቢት 9/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ጎዳናዎችና መንደሮች ውስጥ የሚታየው የረመዳን ወር የአምልኮ ብቻ ሳይሆን የጥልቅ ማኅበራዊ ትስስር መገለጫም ነው።
በተለይም የማፍጠሪያ ሰዓት ሲቃረብ የሚታየው የጎረቤታሞች መተሳሰብ፣ ሙስሊምና ክርስቲያኑን በአንድ ማዕድ የሚያገናኝ የዘመናት የፍቅር ገመድ ሆኖ ቀጥሏል።
ቤት ያፈራውን ለጎረቤት- የወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ ደግነት
ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ የማፍጠሪያ ሰዓታቸው ከመቃረቡ አስቀድሞ ቤት ያፈራውን ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ማለቱን ተያይዘውታል። ወይዘሮ ፋጡማ በሃይማኖታቸው አስተምህሮ መሠረት የማፍጠሪያ ሰዓታቸው ሲቃረብ ወደ ጎረቤቶቻቸው ቤት የመሄድና የመጥራት ልማድ አላቸው።

የወይዘሮ ፋጡማ የረጅም ዓመት ጎረቤት የሆኑት ወይዘሮ አቦነሽ አረጋና ሌሎችም ለማፍጠሪያ የሚሆን ግብዓቶችን ይዘው በመገኘት አብሮነታቸውን ይገልጻሉ። ወይዘሮ ፋጡማ ስለ ሁኔታው ለኤ ኤም ኤን ሲያስረዱ፤ ክርስቲያን ጎረቤቶችም አሉኝ፤ በግቢ ውስጥም ክርስቲያኖች አሉ፤ ከእኔ ጋር በስምምነትና በፍቅር ነው ያለነው።
በዓል በሆነ ሰዓት አብረን እናፈጥራለን። የእነሱን በዓል ሲሆን እንሄዳለን፤ እንኳን አደረሳችሁ ብለን እነሱም እኛ ጋር ይመጣሉ።
ጎረቤቱን እንደራሱ ካልወደደና ካላከበረ አይሆንም ስለሚባል፣ እኛ ተከባብረን ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳይኖር ተሳስረን ነው የምንኖረው።
ከጓደኝነት በላይ የሆነው ቤተሰባዊ ትስስር

የወይዘሮ ፋጡማ ጎረቤት የሆኑት ወይዘሮ አቦነሽ አረጋ በበኩላቸው፣ በጣም ደስ ይላል። ወይዘሮ ፋጡማ ቤት ሁልጊዜ በዓል በሆነ ጊዜ ተጠራርተን ነው የምናፈጥረው።
እሷም የእኛን እምነት ታከብራለች፤ እኛም የእሷን እምነት አክብረን ረመዳን ሲመጣ በፍቅር እናሳልፋለን ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ሌላዋ ጎረቤታቸው ፋንታዩ ወርቁ ደግሞ ግንኙነታቸው ከጓደኝነት አልፎ ቤተሰባዊ መሆኑን እንዲህ ትገልጻለች፦ “ወይዘሮ ፋጡማ የእናቴ የብዙ ዓመት ጓደኛ ናቸው። ሁሌም አፍጥር ሲሆን ይጠሩናል፤ እኛም እንገኛለን። ሰርግም ሲኖር እንጠራራለን፤ ማኅህበራዊ ኑሯችን ጥብቅ ነው።”
ማሜ ማንያዘዋልም ይህንኑ ሲያጠናክሩ፣ ኢትዮጵያዊነት በሚል ሙስሊም ክርስቲያን ሳይባል የእሷም ልጆች መጥተው ይበላሉ ይጠጣሉ፤ የእኔም ልጆች እንዲሁ። ቡና ጠጥተን ያለውን ተቃምሰን በፍቅር 28 ዓመታት ዘልቀናል ብለዋል።

“ሙሃባ” – መለኮታዊ ፍቅርና ማህበራዊ ሰላም
ያሲን ኢብራሂም “ሙሃባ” የሚለውን ጽንሰ-ሀሳብ ከመለኮታዊ ፍቅር ጋር ያገናኙታል።
ሙሃባ ማለት መፈቃቀር ነው። መፈቃቀር ወደ አላህ ዘንድ ያደርሳል። መተዛዘን፣ የሌለውን ማሰብና ካለው ላይ መቀባበል ሃይማኖታችን የሚፈቅደው ትልቅ ተግባር ነው ይላሉ።
ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ቅርስ
ይህ ውብ አብሮነት በህፃናት ልብ ውስጥም ትልቅ ቦታ አለው። ሕጻን መክሊት ጌታቸው እንደምትለው እናቴ ሥራ በምትሆንበት ጊዜ እዚሁ ወይዘሮ ፋጡማ ጋር ነው የምቆየው።
እዚህ መጥቼ አብሬያቸው የምቆይበትና መክሰስ የምበላበት ሰዓት አለ። እነሱ ያላቸው ጉርብትና በጣም ደስ ይላል፤ እኔም አድጌ እንዲህ መሆን ነው የምፈልገው።
የወይዘሮ ፋጡማና የጎረቤቶቻቸው አብሮነት፣ በህፃናት ልብ ላይ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲቀረጽ በማድረግ፣ ነገን በተስፋና በናፍቆት እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ