ሊቨርፑል እና ባየርን ሙኒክ ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜ ደረሱ

You are currently viewing ሊቨርፑል እና ባየርን ሙኒክ ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜ ደረሱ

AMN- መጋቢት 9/2018 ዓ.ም

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ዙር የመልስ ጨዋታዎች ሊቨርፑል እና ባየርን ሙኒክ በግብ ተንበሻብሸው ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል።

በአንፊልድ ጋላታሳራይን ያስተናገደው ሊቨርፑል 4ለ0 አሸንፏል። ዶሚኒክ ሶቦስላይ ፣ ሁጎ ኢኪቲኬ ፣ ራያን ግራቨንበርች እና ሞሐመድ ሳላህ የመርሲሳይዱን ክለብ አራት ግቦች አስቆጥረዋል።

በጨዋታው ፍፁም ቅጣት ምት ያመከነው ሞሐመድ ሳላህ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን ግቦች 50 አድርሷል። በመጀመሪያው ጨዋታ 1ለ0 ተሸንፎ የነበረው ሊቨርፑል በድምሩ የ4ለ1 ውጤት በማስመዝገብ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ቆይታውን አረጋግጧል።

ቀዮቹ በቀጣይ ባለፈው ዓመት ከውድድር ውጪ ያደረጋቸውን ፓሪሰን ዠርማ በሩብ ፍፃሜው ይገጥማሉ። በሌላ ጨዋታ በአልያንዝ አሬና አታላንታን ያስተናገደው ባየርን ሙኒክ 4ለ1 አሸንፏል።

ሀሪ ኬን በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ግብ ሲያስቆጥር ፣ ሌናርት ካርል እና ሊውስ ዲያዝ ሌሎቹን ግቦች አስገኝተዋል። እንግሊዛዊው አጥቂ ሀሪ ኬን በምሽቱ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ግቦቹን ወደ 50 ከፍ አድርገውለታል።

የጀርመኑ ክለብ በአጠቃላይ ውጤት 10ለ2 በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜ የደረሰ ሌላኛው ክለብ ሆኗል። በቀጣይም ከሪያል ማድሪድ ጋር ይጫወታል። በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ቶተንሃም ሆትስፐርስ አትሌቲኮ ማድሪድን 3ለ2 ቢያሸንፍም ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለም።

በመጀመሪያው ጨዋታ 5ለ2 ተሸንፎ የነበረው የለንደኑ ክለብ በአጠቃላይ ውጤት 7ለ5 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል። ጊዜያዊው አሰልጣኝ ኢጎር ቱዶር የመጀመሪያ ድሉን እንዲያስ መዘግብ የረዱ ግቦችን ዣቪ ሲሞንስ (2) እና ራንዳል ኮሎ ሙአኒ ማስቆጠር ችለዋል። ሁሊያን አልቫሬዝ እና ዳቪድ ሀንኮ የስፔኑን ክለብ ሁለት ግቦች ያስገኙ ተጫዋቾች ናቸው። አትሌቲኮ ማድሪድ በሩብ ፍፃሜው ባርሰሎናን ይገጥማል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review