AMN- መጋቢት 9/2018 ዓ.ም
እደሳው ባላለቀው ካምፕኑ 64ሺ ተመልካቾች የታደሙበት የባርሰሎና እና ኒውካስትል ዩናይትድ ጨዋታ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረውበት ተጠናቋል።
የካታሎኑ ክለብ 7ለ2 ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ግን ባርሰሎና ፍፁም የበላይነቱን ወስዷል። በጨዋታው ለባርሰሎና ራፊንሃ እና ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ፖላንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን ግቦች 109 አድርሷል። የ37 ዓመቱ ተጫዋች የሚበለጠው በክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ ብቻ ነው።

ማርክ በርናል ፣ ላሚን ያማል (ፍፁም ቅጣት ምት) እና ፈርሚን ሎፔዝ ተጨማሪ ግቦችን ያስገኙ ተጫዋቾች ናቸው። የ18 ዓመቱ ላሚን ያማል በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ 10ኛ ግቡን ነው ማስቆጠር የቻለው። በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከባዱን ሽንፈት ለተጋፈጠው ኒውካስትልን ዩናይትድ ሁለቱንም ግቦች አንቶኒ ኢላንጋ ማስቆጠር ችሏል።
የመጀመሪያ ጨዋታውን 1ለ1 አጠናቆ የነበረው ባርሰሎና በድምር ውጤት 8ለ3 አሸንፎ የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆኗል። በቀጣይ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ወይም ቶተንሃም ሆትስፐርስ አሸናፊ ጋር የሚፋለም ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ