ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

AMN መጋቢት 10/2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

እንኳን ለዒድ አል ፈጥር በዓል አደረሰን፣ አደረሳችሁ!

በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ዒድ አል ፈጥር የበረከት በዓል ተደርጎ ይታመናል። ሮመዳንም የአላህ (ሱወ) ደግነት የሚገለጥበት፣ ውድ ስጦታዎችን ለሰው ልጆች የሰጠበት ወር ነው። ቁርአን ወደ ምድር የወረደበት፣ ጀሃነም ተዘግቶ የጀነት በሮች የሚከፈቱበት፣ ሁሉም እንደ እምነቱ ጽናትና እንደ አላህ (ሱወ) እዝነት ምናዳዎችን የሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ ዘወትር የሮመዳንና ዒድ አል ፈጥርን መምጣትን በጉጉት ይጠብቃል።

በዒድ አል ፈጥር ከፈጣሪ በረከት የሚቸራቸው የሮመዳንን ወር በፆምና በዱዓ ያሳለፉት ናቸው፤ በበዓሉ መምጣት የሚያደሰቱትም ሮመዳንን በመልካም ተግባር ለማሳለፍ የበረቱ ናቸው። በተቀደሰው ወር ከክፋት የተቆጠቡ፤ ለድኾችና አቅመ-ደካሞች ዘካት የሰጡ፤ የበደሏቸውን ይቅር ለማለት የደፈሩ በሐሴትና በመንሳዊ ኃይል ተሞልተው ለዒዱ ይደርሳሉ። በተቃራኒው ለዱዓ የሰነፉና ለመስጠት የሰሰቱ ከፈጣሪ በረከት አያገኙም።

ከፊታችን ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ ሀገራችንን የዴሞክራሲን ድል የምትቀዳጅበት፣ ወደ ቀጣይ ብሩህ ዘመንዋ የምትሸጋገርበት በር ነው። እንደ ሀገር ለዓመታት ዴሞክራሲን ስንናፍቅ ኖረናል። ጉዞአችን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ነገር ግን ከፈተና በሁዋላ በረከት፣ ከብርታት በኋላ ሐሴት እንዳለ ከሮመዳን ጾምና ከዒድ አል ፈጥር በዓል እንማራለን።

መልካም የዘራ ሰው መልካም ምርት እንደሚያጭድ ሁሉ፤ እሾክ የዘራውም አሜኬላ ያጭዳል። ስለተመኘን ብቻ አሜኬላው በመልካም ሰብል አይለወጥም። በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊ ጉዳዮች ውስጥ ዘርና ምርት የተቆራኙ ናቸው። ስለዴሞክራሲም ስናስብ ይሄንን ሐቅ መዘንጋት የለብንም። የምንገነባው ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት የሚወሰነው በቅድመ ምርጫ ተሳትፎአችን ልክ ነው።

ተሳትፎአችን ከጠየመ ዴሞክራሲያችንም ይጠይማል። ደካማ ተሳትፎ አድርገን ጠንካራ ዴሞክራሲ ለማዋለድ መመኘትም ሞኝነት ነው። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በባዶ መሬት አይበቅልም፤ በግጭትና ሥርዓት አልበኝነትም አይገነባም። ይልቁንም ስክነትን፣ ለትብብርና ቅንጅት ልብን ክፍት ማድረግን፣ በጨዋታው ሕግ መመራትን ይጠይቃል።

ሮመዳን ቤተሰብ የሚገናኝበት፣ ኅሊና የሚሰበሰብበት፣ ሰውነት የሚገራበት እና መንፈስ የሚቀናበት ወር ነው። ዒድ አል ፈጥር ደግሞ የሰውን ልጅ ጤናማ ግንኙነቶች የሚያመለክት በዓል ነው። የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር፣ ከራሱ ጋር እና ከወገኑ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ጤናማ ካልሆነ ጠቅላላ ሕይወቱ ጤናማ አይሆንም። በሮመዳን ወቅት ጾሙ ሰዎችን ከራሳቸው ጋር ያገናኛቸዋል፤ ሰላትና ዱአ ከፈጣሪያቸው ጋር ያገናኛቸዋል፤ አፍጣርና ዘካት ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር ያገናኛቸዋል። ኢትዮጵያውያን ጤናማ ሕይወትን መምራት እንድንችል እነዚህን ሦስቱን ጤናማ ማድረግ አለብን።

ሰው ከፈጣሪው እና ከራሱ ጋር ያለው ግንኙነት ጤናማ ካልሆነ ለማኅበረሰብም ለሀገርም ጠንቅ ነው። ሰው ከራሱ ጋር እየተጋጨ ከኖረ ከሁሉም ጋር ይጋጫል። ዛሬ ጦርነትን ባህል፣ ዝርፊያን ልማድ፣ ጥፋትን ዕሴት፣ ውድመትን ክብር አድርገው የሚኖሩት ሰዎች የመጀመሪያው ችግራቸው ከፈጣሪያቸውና ከራሳቸው ጋር አለመስማማት ነው። ውስጣዊ ባሕርያቱ ያልተስማሙለት ሰው ከማንም ጋር አይስማማም።

ዕርቅ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት እና መስማማት የሚባሉት ነገሮች አይገቡትም።ሰው ከፈጣሪውና ከራሱ ጋር ከተስማማ፣ ከማንም ጋር መስማማት ይችላል። ከእንስሳትም ጋር ሳይቀር። “ለድንቢጥ እንኳን ቢሆን የራራ ሰው፤ በፍርድ ቀን (ቂያማህ) አላህ ይራራለታል” ሲሉ ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተማሩት ለዚህ ነው። የእስልምና ዋናው መሠረቱ ሰላም የሆነው ለዚህ ነው። ሰላም ማለት ከራስና ከአካባቢ ጋር በጤናማ ግንኙነት ለመኖር መቻል ነውና።

የዘንድሮውን የዒድ በዓል ስናከብር በዓለማችን ስለ ሰላም የሚነገረውን ያህል የዓለም ሕዝቦች በሰላም መኖር ለምን አልቻሉም ብለን እንጠይቅ? የግጭትና የጦርነት ድንጋይ እየደጋገመ ለምን ይመታናል? ከአዛኝ ይልቅ ገዳይን እንደ ጀግና የሚያየው ልምምዳችን ለምን ገናና ሆነ? የሰው ልጅ ከግጭትና ከጦርነት ያተረፈው ድህነትና ኋላ ቀርነት መሆኑን እያየን ለምን አልተማረንም? ሠልጥኗል በምንለው ዓለም የሚኖሩ ወገኖቻችን እንዴት ግጭትንና ጦርነትን የሚያበረታቱ ሆኑ? ይህ ትውልድ እነዚህን ጥያቄዎች በሚገባ አጢኖ ምላሽ ሊያገኝላቸው ይገባል።

ከራሳቸው ጋር ሰላም ያጡ አካላት የማኅበረሰቡን ሰላም እንዲረብሹ ልንፈቅድላቸው አይገባም። ከሮመዳን ዕሴቶች ጋር የተጣሉ ሰዎች ዘመኖቻችንን እንዲረብሹ ልንፈቅድላቸው አይገባም። በዐሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መኖር ቀድሞ መገኘት ነው። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እንደ ዐሥራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን መኖር ግን መረገም ነው። መግደል፣ ማገት፣ የገበሬውን እርሻ ማቃጠል፣ ሴቶችን መድፈር፣ ማኅበራዊ ተቋማትን መመዝበር፣ ቅርስና ታሪክን ማበላሸት፣ ጠመንጃን የሁሉም ነገር መድኃኒት አድርጎ መውሰድ፣ እነዚህ ሁሉ ከ800 ዓመታት በፊት ያለፉ የሰው ልጅ ጠባያት ናቸው።

ከሦስት አካላት ጋር የታረቁ ሰዎች ብርቱዎች ናቸው ይባላል፤ ከራሳቸው፣ ከማህበረሰባቸው እና ከፈጣሪያቸው ጋር። እንደ ኢትዮጵያዊ እኛም ራሳችንን የገዛን፣ ፈጣሪን የምንፈራ እና ለማህበረሰብ ሰላምና እድገት የምንጨነቅ መሆን አለብን። ኢትዮጵያ የምታድግና የምትበለጽገው በዜጎችዋ እንጂ በሌላ አይደለም። ዜጎችዋ ሲገነቡ ትገነባለች፤ ዜጎችዋ ሰላም ሲሆኑ ሰላም ትሆናለች፤ ዜጎችዋ ሲስማሙ የብልጽግና ጉዞዋ ይሰምራል።

የኢትዮጵያም መበልጸግ የሌላ ሳይሆን የእኛ መበልጸግ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚፈለግብንን መሥዋዕትነት ሁሉ የመክፈል ኃላፊነት የእኛ ነው። የእኛ ልፋት ከዛሬ አልፎ ለትውልድ ይተርፋል። ሀገር መውደዳችን የሚታወቀው እና መልካም ዜግነታችን የሚገለጠው በሥራችን ነው።

ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) “ምርጥ ሰዎች ማለት ሌሎችን ለመጥቀም የበረቱ ሰዎች ናቸው” ብለው ያስተማሩትም ለዚህ ነው። ይሄን የዒድ አል ፈጥር በዓል እነዚህን መልካም ዕሴቶች እያሰብን፣ ሦስቱን ጤናማ መሥመሮችንም እያጸናን እንድናከብረው አደራ እላለሁ።

በድጋሚ መልካም የዒድ አል ፈጥር በዓል ይሁን!

ዒድ ሙባረክ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መጋቢት ፣ 2018 ዓ.ም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review