የኒውክሌር ቦምብ ምስጢራዊ ታሪክ – ከአንስታይን ቀመር እስከ ኦፐንሃይመር ፕሮጀክት

You are currently viewing የኒውክሌር ቦምብ ምስጢራዊ ታሪክ – ከአንስታይን ቀመር እስከ ኦፐንሃይመር ፕሮጀክት

AMN- መጋቢት 10/2018 ዓ.ም

ስለ ዓለም ትልቁ ስጋት የኒውክሌር ቦምብ ሲነሳ ብዙ ጊዜ ቀድሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የፊዚክስ ሊቁ የአልበርት አንስታይን ስም ነው።

እ.ኤ.አ. በ1905 ያገኘው ዝነኛው የቁስና የኃይል ቀመር ለኒውክሌር ኃይል መፈጠር ሳይንሳዊ መሠረት ቢጥልም፣ ቦምቡ ግን የአንድ ሰው የፈጠራ ውጤት ብቻ አልነበረም። ይልቁንም የበርካታ ሳይንቲስቶች የጋራ ጥረትና የዓመታት የምርምር ውጤት ነው። ይህ ጥፋት አዘል መሣሪያ እውን ሊሆን የቻለው በጄ. ሮበርት ኦፐንሃይመር ሳይንሳዊ መሪነት ነበር።

ኦፐንሃይመር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ የመጀመሪያውን የአቶሚክ ቦምብ ለመሥራት ያካሄደችው የ”ማንሃተን ፕሮጀክት” ዳይሬክተር በመሆን ባከናወነው ተግባር “የአቶሚክ ቦምብ አባት” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ይሁን እንጂ ከእርሱ ጀርባ እንደ ሊዮ ሲላርድ ያሉ የኒውክሌር ሰንሰለታማ ግብረመልስን የነደፉ እና እንደ ኤንሪኮ ፌርሚ ያሉ የመጀመሪያውን የኒውክሌር ሪአክተር በተግባር የገነቡ ታላላቅ ሳይንቲስቶች ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የአንስታይን ስም ከዚህ አጥፊ መሣሪያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው በሁለት ዋና ዋና ታሪካዊ ምክንያቶች ነው። አንደኛው አነስተኛ መጠን ያለው ቁስ ወደ ግዙፍ ኃይል ሊቀየር እንደሚችል በንድፈ-ሀሳብ ማረጋገጡ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ናዚ ጀርመን የኒውክሌር መሣሪያ ሊሠራ ይችላል በሚል ስጋት ለወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት የጻፈው ደብዳቤ ነው።

ይህ ደብዳቤ አሜሪካ የራሷን የአቶሚክ ምርምር እንድትጀምርና “ማንሃተን ፕሮጀክት” እንዲመሠረት መንገድ ከፋች ሆኗል።

የሚገርመው ግን፣ የአሜሪካ መንግሥት “ለሰላም ያለው ጽኑ አቋም እና የፖለቲካ ዝንባሌው ለደኅንነት አስጊ ሊሆን ይችላል” በሚል ስጋት አንስታይን በፕሮጀክቱ ውስጥ በቀጥታ እንዳይሳተፍ አግዶት ነበር።

የጃፓን ከተሞች በቦምብ መመታታቸውን የሰማው አንስታይን በሕይወቱ ከፍተኛ ድንጋጤና ቁጭት ውስጥ ገባ። “በሕይወቴ አንድ ትልቅ ስህተት ብሠራ፣ ለሩዝቬልት ያንን ደብዳቤ መጻፌ ነው” በማለት ተጸጽቷል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቀሪ የሕይወት ዘመኑ ትኩረቱን ወደ ሰላም ጥሪ በመመለስ፣ ከፈላስፋው በርትራንድ ራስል ጋር በመሆን የዓለም መንግሥታት የኒውክሌር ጦርነትን እንዲያስቀሩ የሚጠይቅ “የአንስታይን-ራስል ማኒፌስቶ” ፈርሟል።

በተጨማሪም የኒውክሌር መሣሪያዎች በአንድ ሀገር እጅ ብቻ ከመሆን ይልቅ በዓለም አቀፍ ተቋም ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ በጽኑ ሲሟገት ቆይቷል።

በመጨረሻም፣ የኒውክሌር ቦምብ ስጋትነቱ ከቴክኖሎጂው ጥንካሬ በላይ የሰውን ልጅ ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ላይ ነው።

አንስታይን ይህንን አደጋ ሲያስረዳ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በምን ዓይነት መሣሪያ እንደሚካሄድ አላውቅም፣ አራተኛው ግን በዱላና በድንጋይ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ” በማለት ለዓለም ታላቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ አልፏል።

ዋቢ፦ Institute of Advanced Study, Space.com and History.com


በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review