AMN- መጋቢት 11/2018 ዓ.ም
በዓል ሲመጣ ከረጅም የጾም ወራት ወይም ከተለመደው የኑሮ ዘይቤ ወጥተን “የተፈቀደልንን” ሁሉ የምንመገብበት ወቅት ይመስለናል።
ሆኖም በደስታና በጭብጨባ የሚታጀበው የበዓል ገበታችን፣ አዘገጃጀቱ ካልታወቀ ለጤናችን አሉታዊ ተፅዕኖ ይዞ እንዳይመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
የሥነ-ምግብ ባለሙያዋ ኬብሮን ሰናይ፣ በበዓላት ወቅት የሚዘጋጁ ቅባት የበዛባቸው ምግቦች በጤናችን ላይ ስለሚደቅኑት አደጋና መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲህ ይመክራሉ።
በዓላት የብዙዎቻችንን የአመጋገብ ልምድ በድንገት የሚቀይሩ ወቅቶች ናቸው። ከዚህ ቀደም ስንከተላቸው የነበሩ መልካም ልምዶችን በመተው፣ አዳዲስና ከበድ ያሉ ምግቦችን ለሰውነታችን የምናስተዋውቅበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ይህ ድንገተኛ ለውጥ ለጤናችን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።
በተለይ በእኛ ሀገር ልምድ በበዓል ወቅት የሚዘጋጁ ምግቦች፣ ለረጅም ሰዓት እሳት ላይ የሚቆዩ፣ ለከፍተኛ ሙቀት የሚጋለጡ፣ ከፍተኛ የቅባት መጠን (ዘይት፣ ቅቤና ስጋ) ያላቸው፣ ከመጠን በላይ ጨው የሚገባባቸው መሆናቸው አደጋውን ያከፋዋል።
እነዚህን ምግቦች በአንድ ጊዜ አብዝቶ መመገብ በተለይ ቀደም ሲል የጤና እክል ያለባቸውን ሰዎች ሁኔታ ያባብሰዋል። በተለይ ደግሞ፤ በእድሜ የገፉ አረጋውያን፣ በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የህክምና ክትትል የሚያደርጉ ሰዎች፣ ምግብን መርጠውና ራሳቸውን ችለው ማዘጋጀት የማይችሉ ወገኖች ላይ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል።
የወጥ አዘገጃጀት ሚስጥራዊ የጤና ችግሮች
በአመጋገባችን ውስጥ ወጥ ትልቅ ቦታ አለው፤ ይሁን እንጂ ወጥን በርከት አድርጎ ሰርቶ ደጋግሞ ማሞቅ የራሱ የሆነ የጤና ጠንቅ እንዳለው ባለሙያዋ ይገልፃሉ።
ቅባቱ ደጋግሞ ለከፍተኛ ሙቀት ሲጋለጥ ተፈጥሯዊ ይዘቱን የሚለውጥ ሲሆን፣ ይህ የተቀየረ የቅባት ባህሪ ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ የሆኑ ነገሮች እንዲመረቱ ያደርጋል። ለምሳሌ የዶሮ ወጥን ብንመለከት፤ ዘይቱን አግሎ ሽንኩርትን ማቁላላት የተለመደ ቢሆንም፣ ይህ ሂደት ለረጅም ሰዓት ከሚወስደው ሙቀት በተጨማሪ ተደጋግሞ ሲሞቅ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል።

መፍትሄው
ጣዕምን ከጤና ጋር ማመጣጠን የዘመኑ ቁልፍ ጉዳይ ነው የሚሉት የሥነምግብ ባለሙያዋ፣ ከመፍትሄ ሃሳቦች መካካል፤ ምግቦችን (ሽንኩርትን) መጀመሪያ በውኃ ወይም ያለ ቅባት ማብሰል፣ ቅባትን በመጨረሻ ላይ መጥኖ መጨመር የተሸለ መሆኑን ያስረዳሉ።
የጮማ ጥብስ ለምላስ ቢጣፍጥም፣ ጣዕምን ከጤና ጋር አወዳድሮ መወሰን ይገባል፤ ምግቦች በራሳቸው ውኃ እንዲበስሉ ማድረግና ቅባትን ለጣዕም ያህል ብቻ መጠቀምም ይመክራሉ።
ምንም አይነት የጤና ችግር የለብኝም ብለን ብናስብ እንኳ፣ የበዓል ወቅት የምግብ አዘገጃጀታችንን የምንፈትሽበት ሊሆን ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ