AMN መጋቢት 11/2018
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ የሱፍ ለ1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሊቀ መንበሩ በመልዕክታቸው በመላው አፍሪካ እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሙስሊሞች እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል። የረመዳን ወር ማብቂያ የሆነው ይህ የተቀደሰ ወቅት፤ የማሰላሰያ፣ የምስጋና እና የመታደስ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በዓል እንደ ግጭት፣ መፈናቀል፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና የአየር ንብረት ለውጥ ባሉ ታላላቅ ፈተናዎች ውስጥ በምትገኘው ዓለማችን ውስጥ የርህራሄን፣ የአንድነትንና የልግስናን ዘላቂ እሴቶች ያላቸውን ቁልፍ ሚና እንደሚያስታውስም አመልክተዋል።
ኢድ የተስፋ ጥሪም ጭምር ነው ያሉት ሊቀመንበሩ በሀገራት እና በማህበረሰቦች መካከል ያለውን ትስስር እንዲጠናክር፣ የተቸገሩትን እንድንረዳ፣ እንዲሁም ለሰላም፣ ለፍትህ እና ለሰው ልጅ ክብር በድጋሚ ቃላችን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ከቤተሰቦቻችንና ከምንወዳቸው ጋር ስናከብር፣ ይህንን ቀን በችግር ውስጥ ሆነው የሚያሳልፉትን አንዘንጋ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢድ በዓል ፍትሃዊ፣ ሁሉን አሳታፊና ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት ለምናደርገው የጋራ ጥረት መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሚሆን ሙሉ እምነቴ ነው ብለዋል።