የኢድ ድምቀት የሆነው የሂና ጥበብ

You are currently viewing የኢድ ድምቀት የሆነው የሂና ጥበብ

AMN – መጋቢት 11/2018 ዓ.ም

የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ደመቅ ያሉ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል የሴቶችን የበዓል ውበት ይበልጥ ለማድመቅና ለሂና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተዘጋጀው ባዛር አንዱ ነው።

የሂና ጥበብ ወደ አምስት ሺህ ዓመታት ገደማ የሚጠጋ ረጅም ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ከጥንታዊት ግብፅ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት ሲዘወተር የቆየና በአሁኑ ወቅትም በሀገራችን ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ የመዋቢያ ጥበብ ነው።

የባዛሩ አዘጋጅ ሃቢባ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ ባዛሩ የተዘጋጀው በቤታቸው ሆነው ሂና የመሥራት አቅምና ፍላጎት እያላቸው ነገር ግን የሥራ ቦታ ምቾት ያላገኙ ሴቶችን ለማበረታታት ነው።

በቤታቸው ውስጥ የሚሠሩ ሴቶችን በመሰብሰብና እንዲህ ዓይነት ቦታ በማዘጋጀት፣ ለበዓሉ ለራሳቸው የሚሆን ገቢ እንዲያገኙና እንዲበረታቱ አስበን ነው ያዘጋጀነው” ብለዋል አዘጋጇ።

እንዲሁም ደንበኞች በሂና ቤቶች ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ረጅም ወረፋና እንግልት ለማስቀረት ባዛሩ ትልቅ መፍትሔ ይዞ መምጣቱ ተገልጿል።

የሂና ባለሙያዋ ሀሰና ሱልጣን እንዲህ ዓይነቱ መድረክ መፈጠሩ ለባለሙያዎቹ ትልቅ ዕድል መሆኑን ስትገልጽ፣ ሌላዋ ባለሙያ ሂክማ ጀማል ደግሞ “ባዛሩ ከጠበቅነው በላይ ስኬታማ ነው፤ የበዓል ወከባን በመቀነስ ለብዙ ሴቶች ዕድል ፈጥሯል” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

ባዛሩን ጎብኝተው አገልግሎት ያገኙ ተጠቃሚዎችም በዝግጅቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል፣ ማርየም ማህመድ ረጅም ወረፋ ባለመኖሩና ጥሩ አድርገው ስለሠሩልን የበዓሉ ድባብ ከጠበቅኩት በላይ ደስ ይላል ብላለች።

ሪሃና ዲኑየተባለችው ተጠቃሚ ደግሞ ቀደም ሲል ለሰዓታት እንጠብቅ የነበረውን ወረፋ እንዳስቀረላቸው ተናግራለች፡፡

በዚህ ባዛር የሂና ሥራ ዋጋ እንደ ዲዛይኑ ዓይነት የሚለያይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ300 ብር ጀምሮ እስከ 600 ብር ባለው ዋጋ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል። የባዛሩ አዘጋጆች ከዚህ በኋላም ባዛሩ በየበዓላቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review