“በረመዷን ወር የተላበሳቸውን መልካም ስነ ምግባራት ከረመዷን በኋላም ማስቀጠል አለበት”
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዷን ወር የተላበሳቸውን መልካም ሥነ ምግባራት ከረመዷን በኋላም ማስቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
ይህ ጥሪ የቀረበው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ1 ሺህ 447ኛውን የኢድ አል ፊጥር በዓል አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይህ አብዱልከሪም ሸይህ በድረዲን በመግለጫው ላይ እንዳሳሰቡት፣ “ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዷን ወር የተላበሳቸውን መልካም ሥነ ምግባራት ከረመዷን በኋላም ማስቀጠል አለበት” ብለዋል።
በዓሉን ስናከብር በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በመደገፍና በመርዳት ሊሆን ይገባል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዷን ወር የተላበሳቸውን መልካም ሥነ ምግባራት ከረመዷን በኋላም በማስቀጠል ዒዱን በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በደስታ ሊያከብር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የአስተዳደር ጉዳዮች እና የተቋማት ልኅቀት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ተምኪን አብዲላሂ በበኩላቸው፣ በኢስላማዊ አስተምህሮ መሠረት በኢድ ቀንም ሆነ ከኢድ በኋላ እኛ በልተን እያደርን ጎረቤቶቻችን ተርበውና ተከፍተው ሊውሉና ሊያድሩ አይገባም ብለዋል።
በተያያዘም የታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማም ሐጂ ጠሃ ሀሩን በትናንትናው ዕለት የ1 ሺህ 447ኛው የኢድ አል ፊጥር በዓል አከባበር እና የሶላት ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከናወነበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ሀገር እንድትሆን እያንዳንዱ ዜጋ በአብሮነት መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በዓሉ በጁምዓ ቀን መዋሉ ልዩ በረከት እንዳለው የጠቆሙት ሐጂ ጠሃ፤ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ዱዓ በማድረግና የሸዋልን ስድስት ቀናት በመጾም መንፈሳዊ ጥንካሬን ማሳደግ እንደሚገባም አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ትናንት የ1 ሺህ 447ኛው የኢድ አል ፊጥር በዓል አከባበር እና የሶላት ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ ስታዲየምና በዙሪያው በሚገኙ ጎዳናዎች በታላቅ ድምቀት ሲከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ ሌሎች የእምነቱ አባቶች፣ የውጭ ሀገር አምባሳደሮች እንዲሁም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡
በይግለጡ ጓዴ