ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ምን ተሰርቷል?

You are currently viewing ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ምን ተሰርቷል?

በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ መስተጓጎል ተከስቷል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በዚህም ምክንያት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በእጅጉ እየተፈተነ ይገኛል። ሀገራት ችግሩን ለመቋቋም አዳዲስ የነዳጅ አቅርቦት አማራጮችን ከመፈለግ ባሻገር፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት የመጠቀምና የተለያዩ የቁጠባ ዘዴዎችን የመዘርጋት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት፦ “በመካከለኛው ምሥራቅ በተፈጠረው ቀውስ የተነሣ ነዳጅ ገዝተው የሚጠቀሙ ሀገሮች እንደልብ ለማግኘት ተቸግረዋል። በመሆኑም ችግሩ ተፈትቶ ወደ መደበኛው የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት እስክንመለስ ድረስ ነዳጅን በቁጠባና ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት መጠቀም ይኖርብናል” ሲሉ ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት ችግር እስኪፈታ ድረስ ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም ነዋሪዎች አጫጭር መንገዶችን በእግር በመጓዝ፣ እንዲሁም የብስክሌት አማራጮችን እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ትብብር እንዲያደርጉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት የሚያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት፣ ብክለትን ለመቀነስ እና ሀገሪቱ ነዳጅ ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መጠን ለመቀነስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትን እና አስመጪዎችን ማበረታታትን ጨምሮ፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖሊሲ አቅጣጫ መከተል ከጀመረች ዋል አደር ብላለች፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ከዚህ ባለፈ ነባርና ዕድሜ ጠገብ የሆኑ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የመቀየር ሥራም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም የትራንስፖርት ዘርፉን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ ከ100 በላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶብሶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንደ ባሕር ዳር፣ አዳማና ጎንደር ባሉ የክልል ከተሞችም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶብሶች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ  ተሽከርካሪዎች የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ መሠረተ ልማቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የግሉ ዘርፍ በስፋት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በኮሪደር ልማት የተሽከርካሪዎች፣ የእግረኞችና የብስክሌት መንገዶችን በመገንባትና በማስፋት ነዋሪዎች ሞተር አልባ የብዝኃ ትራንስፖርት አማራጮችን እንዲጠቀሙ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከማጠናቀቅ በተጨማሪ የነፋስ፣ የፀሐይና የጂኦተርማል ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በማስፋፋት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት መሠረት እየጣለች ትገኛለች። መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎችና ነዳጅን በቁጠባ የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንደ ሀገር ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያመጡ እንደሆነ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ በዓለም ላይ የነዳጅ አምራችና ላኪዎች ማኅበር (ኦፔክ) የነዳጅ አቅርቦትና ዋጋን ከፍና ዝቅ በማድረግ የሚወስኑበትንና ጫና የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ለመቀነስ ሀገራት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ወደ መጠቀም ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥና የዋጋ መጨመር ሲታይ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት ላይ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ያሳያል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለች የኃይል ፍላጎቷን በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ በመመስረት ለምታሟላ ሀገር በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት በጣም አዋጪ መንገድ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪናዎችን ለማበረታታት ባደረገው ጥረት አሁን ላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል መኪኖች በብዛት ሲንቀሳቀሱ እየታየ ነው፡፡ ይህ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያ በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት አቃልሏል፡፡ ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል ከነዳጅ ጥገኝነት እንድትወጣ መሥራት እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ሞላ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከሰሞኑ “የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ኤሌክትሪክና የተፈጥሮ ጋዝ የማሸጋገር እና የነዳጅ ቁጠባ ሀገራዊ ጥሪ” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ እንዳብራራው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የነዳጅ ቀውስ ለመሻገር መንግሥት አስቀድሞ ከነዳጅ ጥገኝነት የሚያላቅቁና ዘላቂ ሀገራዊ ጥቅምን የሚያመጡ አዳዲስ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅና የራሷን የተፈጥሮ ጸጋ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የዓለም የነዳጅ ገበያ ለከፍተኛ አደጋ መጋለጡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአራት ዓመታት በፊት የነዳጅና የሌላ ማበረታቻ እንዲያገኙ ያደረጉት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፖሊሲ ዛሬ ላይ ሀገርን ከፈተና የሚታደግ ብልህ እና አርቆ አሳቢ ውሳኔ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል፡፡

ሚኒስቴሩ ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋም እና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመታደግ በሚከተሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በመንግሥት እና በግል ተቋማት ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀምን እንደ ሀገራዊ ባህል ማዳበር፣ በነዳጅ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በመተው የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙ ማስቻል፣ በነዳጅ የሚሠሩትን ወደ ኤሌክትሪክ እና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ሥራን ማጠናከር፣ እንዲሁም እስከ 20 ቶን የሚይዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ፤ ከ20 ቶን በላይ የሆኑት ደግሞ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ መንግሥት እና የግል ዘርፍ በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡

ባቡሮችን፣ አውቶብሶችን እና ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በስፋት እና በአግባቡ መጠቀም፤ አገልግሎቱም በወጣለት ታሪፍ እና መርሐ-ግብር ያለ መቆራረጥ እንዲሰጥ በትብብር መሥራት እንዲሁም ከተሽከርካሪ አጠቃቀምና አነዳድ ባህል ለውጥ ጋር በተያያዘ ከአንድ ቤት ውስጥ ብዙ መኪናዎችን ይዞ መንገድ ከመውጣት ይልቅ በጋራ የመጠቀም ልምድን ማዳበርና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ፤ ይህም የውጭ ምንዛሬ ለማዳን፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ዜጎች በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ እንዳይጎዱ ለማድረግ እንደሚያስችል ሚኒስቴሩ ጠቁሟል፡፡

መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት የወሰደው እርምጃ በአሁኑ ወቅት ላጋጠመው ቀውስ ምላሽ በመሆን ቀላል የማይባል እፎይታ እንደሚሰጥ ያነሱት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ሞላ (ዶ/ር)፤ ከዚህ ባሻገር ሙሉ በሙሉ ከነዳጅ ጥገኝነት የመውጣቱ ሂደት ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ አሁን ያጋጠመውን የነዳጅ አቅርቦት ችግርና ጫና ለመቀነስ ነዳጅን በቁጠባና አስፈላጊ ለሆነ ጉዳይ ብቻ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ አሁን ያጋጠመውን ችግር ለመሻገር ተሽከርካሪዎችን አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች እና የሕዝብ ትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም ይገባል፡፡ ዜጎች በእግር እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ ሳይክልና የተለያዩ ሞተር አልባ ትራንስፖርቶችን እንዲጠቀሙ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አክለው ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዥ በየዓመቱ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች። መንግሥት በመቶ ቢሊዮን ብር በጀት ድጎማ እያደረገ ለኅብረተሰቡ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና ድጎማ የሚቀርበው ምርት በገበያ ላይ ከተቀመጠው በላይ በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጠ በመሆኑ፣ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የመንግሥትና የተለያዩ አካላትን በሕግ ቁጥጥር ሥር በማዋል ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር የነዳጅ አቅርቦት አስተማማኝ እንዲሆንም መንግሥት አጣዳፊ ግዥዎች እየፈጸመና ከዲፖዎችም እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ያለውን የነዳጅ ሀብት በከፍተኛ ቁጠባና ኃላፊነት መጠቀም ይገባል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review