የኢድ አልፈጥር የበጎነት እሴት

You are currently viewing የኢድ አልፈጥር የበጎነት እሴት

                                                         በለምለም አምባ መስጂድ ዋና ኢማም ሼህ አሊ መኮንን

ወጣት ጀዋር ሱልጣን በአዲስ አበባ ቤተል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ በቤተል ተቅዋ መስጂድ የወጣት ማህበር ኃላፊ ነው፡፡ “ኢድ አልፈጥር በጉጉት የሚናፈቅና የሚጠበቅ የደስታ በዓል ነው፡፡ በዓሉን በሶላት፣ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ፣ ከሰፈር ነዋሪዎች ጋር በመጠያየቅና አብሮ በመብላት እንዲሁም በደስታ ነው የማሳልፈው፡፡ ከዚህ ባሻገር በጎረቤትና በሰፈር የሚኖሩና በኑሮ አቅም የሚያንሳቸው ወገኖች፣ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን በተለያዩ መልኩ ድጋፍ እናደርጋለን” ሲል ተናግሯል፡፡

በእስልምና ማንኛውም ሰው በቤተሰቡ ቁጥር ልክ ዘካ ማውጣት ወይም መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ይህም አቅም ለሌላቸው ወገኖች የሚሰጥና በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማስቻል ታስቦ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ወጣት ጀዋር እንደሚገለፀው፣ እንደ ተቅዋ መስጂድ አማኙ ዘካ የሚያዋጣ ሲሆን የተሰበሰበውን አቅም ለሚያንሳቸው ሰዎች በአግባቡ እንዲዳረስ የማስተባበር ስራ ይሰራል፡፡ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ የሚወጣውን ዘካ በገንዘብ ተቀብሎ እህል (ዱቄት) ከገበያ በመግዛት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲዳረስ ያደርጋሉ፡፡

ወጣት ጀዋር በእንደዚህ ዓይነት በጎ ስራ ከአስር ዓመት በላይ ሲሳተፍ መቆየቱንና ይህን በማድረጉም እርካታና ደስታ እንደሚሰማው ይናገራል፡፡ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ፣ መተዛዝን፣ መተባበር፣ በጋራ መሆን በእስልምና ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና የሚበረታታ እሴት ነው። በኢድ አልፈጥር የሚከናወነው የዘካ ስርዓትም ቀጣዩ ትውልድም የመዋደድ፣ የመደጋገፍና የመተባበር እሴትን እንዲማር ያደርጋል፡፡ ምቀኝነት ያጠፋል፤ በማህበረሰብ መካከል ሰላምን ያመጣል ሲል የዘካን ፋይዳ ያብራራል፡፡

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ዑስማን አብዱ ኢድ አልፈጥርን ጨምሮ በበዓላት ሁሉም ሰው በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፍ ዘካ ከማውጣት ጀምሮ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በማሰራጨት እንደሚሳተፍ ይናገራል፡፡ በሚኖርበት አካባቢ የሚገኘው የቤተል ተቅዋ መስጂድ የሚታወቅና በርካታ ቁጥር ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች የሚሰግዱበት እንደመሆኑ፣ ከአማኙ ዘካ በመሰብሰብና ዱቄት በመግዛት ድጋፍ ለሚፈልጉ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ያሰራጫሉ፡፡ ይህም በየዓመቱ ኢድ አልፈጥር በመጣ ቁጥር በአደባባይ የሚከናወን እንደሆነ ይናገራል፡፡

ወጣት ዑስማን እንደገለፀልን፣ በረመዳን ወር በየቀኑ በቤተል አደባባይ ማታ ላይ በአፍጥር ሰዓት ለምስኪኖች (አቅመ ደካሞች) ምግብ በማቅረብ እንዲያፈጥሩ ይደረጋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያም የተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ ሀብት በማሰባሰብና በማዳረስ አግማስ ኢትዮጵያ እና ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመሆን ተሳትፎ አድርጓል፡፡

“የተፈጠርኩት ለአላህ ለመገዛት ነው። ለአምላክ የምገዛበት አንደኛው መንገድ ለተቸገሩ ሰዎች መድረስና መኖር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በኪሴ ገንዘብ ካለ በገንዘብ፣ ከሌለ ደግሞ በጉልበትና በእውቀት ሰዎችን መደገፍ ያስደስተኛል፡፡” ሲልም  በበጎነት ስራዎች ላይ ለምን እንደሚሳተፍ ይገልጻል፡፡

“ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፤ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” እንደሚባለው በቤተሰብ፣ በሰፈርና በአካባቢ ብሎም እንደሀገር የሚታዩትን ማህበራዊ ችግሮች እንደ ህዝብ ብንጋራቸው ቀላል ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም ከራሱ ባሻገር ለሌላ ሰው መድረስ ይኖርበታል፡፡ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በእውቀት፣ በጉልበትና በሀሳብ ለሰዎች ጥሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም አብሮ ለማደግ፣  እንደሀገር ችግሮችን ለማቃለልና ወደ ፈጣሪ ለመቅረብ የሚጠቅም ባህል ልናደርገው እንደሚገባ ወጣት ዑስማን ይናገራል፡፡

የረመዳንን ወር የእስልምና እምነት ተከታዮች በጾምና ሰላት፣ በምስጋናና በልግስና ያሳልፋሉ፡፡ በጾም መጨረሻ እና በሸዋል ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ የኢድ-አልፈጥር በዓል በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ የኢድ በዓል በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በጋራ በመስገድ እና የአላህን ስም በማውሳት (በተክቢራ) ይከበራል። በቤት ውስጥ፣ በሰፈር ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት ከወዳጅ ዘመድ ጋር በመሆን በሃላል ምግብና መጠጥ በአንድነትና በጋራ በደስታ ይከበራል፡፡

በኢድ በዓል ከሚከናወኑ ስነ ስርዓቶች መካከል ለአቅመ ደካሞችና ድኻዎች መለገስ (ዘካ) አንዱ ነው፡፡ ሼህ አሊ መኮንን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሚገኘው ለምለም አምባ መስጂድ ዋና ኢማም ናቸው፡፡ ዘካ ከእስልምና እምነት አምስት መሰረቶች መካከል መስጠት አንዱና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ዘካ ሁለት ዓይነት መልክ አለው፡፡ በኢድ አልፈጥር ዋዜማ እና እለት የሚሰጥ የማፍጠሪያ ስጦታ “ዘካቱል ፊጥር” ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ማንኛውም ጿሚ የሆነ የእስልምና እምነት

ተከታይ ሊተገብረው የሚገባ ስርዓት እንደሆነ ሼህ አሊ ያስረዳሉ። “ዘካቱልማል” ሁለተኛው የዘካ ዓይነት ሲሆን በገንዘብ መልክ የሚወጣ ነው። አንድ ሰው ያለው ገንዘብ ፍላጎቱን ከማሟላት ባሻገር ተቀማጭ ከሆነና ተቀማጩ ገንዘብ ከአንድ ዓመት በላይ የቆየ ከሆነ ባለገንዘቡ ዘካ የማውጣት ግዴታ አለበት፡፡ ይህም ባለሀብቶችን የሚመለከት ሲሆን በማንኛውም ጊዜ የሚከናወን ነው፡፡ አብዛኛው ሙስሊሞች የረመዳን ፆም ወቅቱን ጠብቀው ያወጣሉ። በጾም ወቅት የሚሰጥ ዛካ የሚያስገኘው ምንዳ (አጅር) እጥፍ ድርብ ነው፡፡

የረመዳን ጾም ሲፈታ የሚከናወነው ዘካቱል ፊጥር (የሚሰጠው ምጽዋት) ማንኛውንም ሙስሊም ገና የተወለደ ህጻን ልጅ፣ በኑሮ አቅመ ደካማ የሆነ፣ ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይባል ሁሉም ሰው ሳይቀር በራሱና በቤተሰቡ ቁጥር ዘካቱል ፊጥር ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ችግረኛ ሆኖ ዘካቱል ፊጥር ያወጣ ሰው፤ ከሌላ ሰው ዘካ መቀበል ይችላል፡፡

አንድ ሰው 2 ኪሎ ግራም ተኩል ዋጋ ያለው እህል (ስንዴ፣ በቆሎ፣ ቴምር፣ ገብስ ወይም ሌላ) መግዛት የሚችል ገንዘብ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ዘካ መስጠት የእስልምና መሰረት በመሆኑ ዘካ አለማውጣት ከእስልምና መሰረት እንደመውጣት እንደሚቆጠር ሼህ አሊ ያስረዳሉ፡፡

ዘካ መቀበል ያለባቸው ወይም የሚሰጣቸው ድኻዎች፣ በአካል ጉዳት፣ በህመምና በተለያየ ምክንያት ሰርተው መብላት የማይችሉ (ምስኪኖች)፣ ከሌላ እምነት ወደ እስልምና የገባና ችግር ያለበት፣ ዕዳ ኖሮበት እዳውን መክፈል ላልቻለ (በማጣት) እና ሌሎችን ያካትታል፡፡

ሼህ አሊ እንደሚያስረዱት፣ የዘካ ዓላማ በቅርብ የሚደግፋቸው የሌላቸውና ድሃዎች በአቅም ማነስ ምክንያት ቤታቸውን ዘግተው እንዳይውሉ፣ እንዳይተክዙ፣ ገንዘብ ማጣት እንደ ነውር ተደርጎ እንዳይታይ፣ በማጣታቸው እንዳይሰበሩ የሚጠግን፣ የህብረተሰቡ አንድ ወገን መሆናቸውን ለማሳየት የሚሰጥ ምጽዋት ነው። ለችግረኞችና ድሃዎች ዘካ መስጠት በፈጣሪ (አላህ) ዘንድ ደስታ ይፈጥራል። ከሞት በኋላ ባለው ህይወትም ድሃን በመርዳት ግዴታውን የተወጣ ጥሩ ቦታ ይጠብቀዋል፡፡

በኢድ አልፈጥር ወቅት ልጆች አዲስ ልብስ እንዲገዛላቸው ይፈልጋሉ፡፡ አቅም የሌላቸው ለልጃቸው ልብስ፤ መማሪያ ደብተርና እስክርቢቶ መግዛትና ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ይቸገራሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ሀብት ያለው ችግረኛው ሳይናገር በህሊና ተረድቶ፣ ‘የማን ልጆች ናቸው በማጣት ቀልባቸው የተሰበረው’ በማለት በቶሎ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ነገ በተጨነቁ ሰዓት አላህ እንዲደርስላቸው ያደርጋል፡፡ በአዲስ አበባ በዘካ በሚሰጣቸው ገንዘብ ልጆቻቸውን ልብስ የሚያለብሱ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ሼህ አሊ ያነሳሉ፡፡

ሼህ አሊ እንዳሉት፣ በእስልምና ዘካ ድሆች በማጣታቸው የማይተክዙበት፣ ሀብታሞች በማግኘታቸው የማይኮፈሱበት፣ በሀብታሞች ንብረት ላይ የድሀዎች ሀብት ያለበት መሆኑን የሚያስተምር ጥሩ የሆነ የመረዳዳት ልምድ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የእስልምና እምነት ተከታዮች የዘካ ግዴታቸውን በስፋት የሚወጡ ሲሆን ይህም ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብን በማስረፅ፣ ፍቅርን፣ መግባባትን በማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ሼህ አሊ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍ ችግረኞች በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ሀብት በማሰባሰብና የተሰባሰበውን በማሰራጨት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። በለምለም አምባ መስጂድ የሚገለገሉ የእምነቱ ተከታዮች ዘካ ለማሰባሰብ በሚዋቀረው ኮሚቴ ወጣቶች አባል በመሆን፣ ከማህበረሰቡ በተሰበሰበው ገንዘብ ከዱቄት ፋብሪካዎች ዱቄት ይገዛሉ፡፡ ችግረኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲመዘገቡ ከተደረገ በኋላ እንደተገዛው የዱቄት መጠን አስር ወይም አምስት ሊሆን ይችላል፤ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በወጣቶች አማካኝነት ይታደላል፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው የኢድ በዓል እስከ 20 ኩንታል ዱቄት ተሰባስቦ ድጋፍ ፈላጊ ለሆኑ ዜጎች እንዲሰራጭ በማድረግ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ተደርጓል፡፡ በዘንድሮ በዓልም ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በኢድ አልጥር በዓል የሚደረገው የመደጋገፍ እሴት በእለት ተለት ህይወት ሊተገበር እንደሚገባ ሼህ አሊ ይናገራሉ፡፡ “ዘካ መስጠት ግዴታ ነው፡፡ የሰዎችን ማህበራዊ ችግር ያቃልላል፡፡ የነብዩ መሐመድ  መርህንም መከተል ነው፡፡ የእርሳቸው መርህ አንዱ ለአንዱ ማዘን ነው፡፡ ለሰው የማያዝን  ከእኔ አይደለም፤ አላህ አያዝንለትም” ብለዋል፡፡ ይህንንም ህዝበ ሙስሊሙ እንዲተገብረው ማታ ከሶላት በፊት በየመስጂዱ ትምህርት ይሰጣል፡፡

አቅም የሚያንሳቸው፣ በችግር ምክንያት ደስታ የራቀቸው ሰዎች፣ ራሳችን ደስታ እንዳገኘን ሌሎችም ደስ እንዲላቸው ትንሽና ትልቅ ሳይል የዘካ ግዴታውን መወጣት ይኖርብናል፡፡ ነብዩ መሐመድ ‘በአንተ ቤት ደስታ ኖሮ በጎረቤትህ ከሌለ፤ በቤትህ እየበላህ፤ ጎረቤትህ የሚራብ ከሆነ አንተ ከእኔ አይደለህም፤ ነገ በአላህ ዘንድ ያስቀጣል” እንዳሉት በተግባር መገለጥ እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በጥቅሉ ዘካ ከራስ በፊት ለሌላው ማሰብን የሚያስተምር ሥርዓት ነው። እንዲህ ዓይነት እሴቶች አካል ጉዳተኞችን፣ ድኾችን፣ ዐቅመ ደካሞችን፣ አረጋውያንን፣ ሕጻናትንና የተለያዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊ ችግሮች በማቃለል ትስስርን፣ መደጋገፍንና መተባበርን የሚያጠናክር በመሆኑ ትውልዱን በማስተማር አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review