በሦስተኛው ዙር የስራ ላይ ልምምድ የተሳተፉ ወጣቶች መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ይመረቃሉ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው የሥራና ክህሎት ቢሮ፣ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተተገበረ ያለው “ብቃት” የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ያለሥራ የተቀመጡ ወጣቶችን የሥራ ባለቤትና የቤተሰብ ደጋፊ እያደረገ ይገኛል።
የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር፣ ለመዲናዋ ወጣቶች ሁነኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሆኖ ስለማገልገሉ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የመርሃ ግብሩ የሁለት ዙር ፍሬያማ ውጤቶች ምስክር ናቸው፡፡ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ለጉዳዩ ተገቢ ሽፋን ሰጥቷል። በዚህም በሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር የታቀፉ ወጣቶች፡- ከሥራ አጥነት ተላቅቀው፣ የነበረባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጫና አስወግደው፣ ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል ተሸጋግረው፣ ተስፋ መቁረጥን በሥራ ስለት ቆርጠው፣ ዛሬን በጥረት ነገን በተሻለ ርዕይ ቀርፀው… ጉዞ ወደ ፊት የሚል ወኔን የተላበሱ የተግባር ሠዎች መሆናቸውን ከአንደበታቸው ሰምቷል፤ በሥራ ቦታቸው ተገኝቶ ተምልክቷል፤ በአሠሪ ድርጅቶች ምስክርነትም አረጋግጧል፡፡ በሦስተኛው ዙር ተሳታፊ የሆኑ ከስምንት ሺህ የሚልቁ ወጣቶችም፤ በተመሳሳይ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና መልካም የሥራ ሥነ ምግባር የተላበሱ ትንታግ የሥራ ሰዎች ለመሆን የበቁበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ፡፡
ወጣት ገነት ረጋሳ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የአልባሳት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥራ የምትሠ ወጣት ናት። ገነት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት የሚያስችል ውጤት ባለማምጣቷ ምክንያት ተስፋ ቆርጣ በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገድዳ ነበር። “በሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ከመታቀፌ በፊት ምንም ዓይነት ሙያም ሆነ ሥራ አልነበረኝም” የምትለው ገነት፣ ስለ መርሃ ግብሩ መረጃ እንደሰማች ወዲያውኑ መመዝገቧን ታስታውሳለች።
በመርሃ ግብሩ አማካኝነት የተለያዩ ስልጠናዎችን የወሰደችው ወጣት ገነት፣ በራሷ ምርጫ ወደ አልባሳት ኢንዱስትሪ ተቀላቀለች። በሦስት ወራት የሥራ ላይ ልምምድ ቆይታዋም ጨርቅ መቁረጥ፣ ኦቨርሉክ ማድረግ እና መስፋት የመሳሰሉ መሠረታዊ ሙያዎችን በሚገባ ተክናለች። “የሥራ ላይ ልምምድ እንዳጠናቀቅሁ ድርጅቱ በቋሚነት ቀጠረኝ፤ አሁን በወር 5 ሺህ 500 ብር ደመወዝ ይከፈለኛል” በማለት በኩራት ትናገራለች። ገነት አክላም አብዛኞቹ ወጣቶች በመንግስት ተቋማት መቀጠርን ብቻ እንደሚጠብቁና ይህ ሳይሳካ ሲቀር ተስፋ እንደሚቆርጡ ጠቁማ፣ በየአካባቢው ያሉ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚገባ ትመክራለች። በቀጣይም ከምታገኘው ገቢ በመቆጠብ የግል ሥራዋን የመጀመር ትልቅ ህልም እንዳላት ገልፃለች።
በተመሳሳይ ወጣት ቤተልሔም ኪዳነማርያም፣ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ለስድስት ወራት ያለ ሥራ በቤት ውስጥ መቀመጧ ለከፍተኛ ድብርትና ጭንቀት ዳርጓት እንደነበር ትገልጻለች። “እነዚያ ጊዜያት በጣም ረጅምና አሰልቺ ነበሩ” የምትለው ቤተልሔም፣ በሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብሩ አማካኝነት ወደምትወደው የአልባሳት ሙያ በመቀላቀሏ፣ ዕድሉ ከህልሟ ጋር ለመገናኘት እንደድልድይ እንደጠቀማት ትናገራለች። አሁን ላይ ስፌት የመስፋትና ፓተርን የማውጣት ሙያን ተክናለች፡፡ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥታለች፡፡ ሙያዊ ክህሎቷን፣ ዕውቀቷንና የሥራ ሥነ ምግባሯን ከማሻሻሏ በተጨማሪ፣ ከድርጅቱ ባለቤቶች ያገኘችው ልምድ ለቀጣይ ህይወቷ ትልቅ መሠረት ሆኗታል።
የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በአልባሳት ዘርፍ ብቻ የተገደቡ አይደሉም። ከአውቶሞቲቭ ወይም ከተሽከርካሪ ጋር የተያያዘ ሙያን በሚጠይቁ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሠማሩም ብዙዎች ናቸው፡፡ ወጣት ቤዛዊት ጥላሁን ከእነዚህ መካከል አንዷ ናት፡፡ በትምህርት ዝግጅቷ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ገብታ በኤሌክትሪክ ሙያ ብትሰለጥንም ያለሥራ በቤት ለመቀመጥ ተገድዳ ነበር። ገና ከጅምሩ በአውቶሞቲቭ ዘርፍ መሰማራትን ውስጣዊ ፍላጎቷ አድርጋ ቆይታለች፤ ለዚህም ይረዳት ዘንድ ተያያዥ ሙያን በኮሌጅ ገብታ ሰልጥናለች። ይሁን እንጂ ፍላጎቷ እንዲሰምር ትልቁን ድርሻ የተወጣው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር መሆኑን አልሸሸገችም፡፡
“የሥራ ላይ ልምምድ እንዳደርግ በፍላጎቴ መሰረት የተመደብኩበት የኤክራም አውቶሞቲቭ ድርጅት መሆኑን ሳውቅ ህልሜ እውን መሆን እንደጀመረ ተረዳሁ፡፡ ምክንያቱም ድርጅቱ በከተማችን ካሉ ታዋቂ የአውቶሞቲቭ ተቋም አንዱ ነው፡፡ ወደ ድርጅቱ ለጥገና የሚመጡት አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች ዘመናዊና ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚጠይቁ በመሆናቸው አቅሜን በሚገባ አሳድጌያለሁ፡፡ በሥራ ላይ ካሉ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ፡፡” ትላለች። ዛሬ በ4 ሺህ ብር ደመወዝ ተቀጥራ የምትሠራው ቤዛዊት፣ ወጣቶች ሥራ ሳይመርጡና ሳይንቁ መጀመር እንዳለባቸው መልዕክቷን አስተላልፋለች።
በሌላ በኩል፣ ወጣት ዘውዴ መሃመድና አራት ጓደኞቿ በጋራ በመሆን የራሳቸውን የሴቶች ፀጉር ቤት ከፍተው ወደ ሥራ ገብተዋል። ቀደም ሲል ሥራ አጥና ክህሎት አልባ የነበሩት እነዚህ ወጣቶች፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት እና ልምምድ ባደረጉበት ድርጅት ድጋፍ አማካኝነት ዛሬ የሥራ ባለቤት ሆነዋል። የክፍለ ከተማው አስተዳደር የአንድ ወር የቤት ኪራይ የከፈለላቸው ሲሆን፣ የልምምድ ድርጅቱ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችንና ግብዓቶችን አሟልቶላቸዋል። “ተቀጥረን ለመሥራት እናስብ የነበርን ወጣቶች የራሳችንን ሥራ መጀመር ችለናል” በማለትም የጅምራቸውን ስኬታማነት ገልጸዋል።
የዮኬት ማኑፋክቸሪንግ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛዊት ነጌሶ፣ መርሃ ግብሩ ለድርጅታቸውም ትልቅ ጥቅም ማምጣቱን ይናገራሉ። ድርጅታቸው 30 ተለማማጅ ወጣቶችን በመቀበል በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ልምምድ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ወደ ድርጅቱ የገቡት ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ ልምምዱን በሚገባ በማጠናቀቃቸው፣ ሙያዊ ክህሎትንና የሥራ ሥነ ምግባርን በመላበሳቸው ሁሉም በድርጅቱ በቋሚነት መቀጠር ችለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን የሰጡት ወጣት ገነት ረጋሳ እና ወጣት ቤተልሔም ኪዳነማርያም እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጇ፤ “ወጣቶቹ በሙያ ብቁና በሥራ ሥነ- ምግባር የታነጹ ናቸው፤ በመካከላችን በነበረው መልካም ግንኙነት በ15 ቀናት ውስጥ ወደ ማምረት ሥራ መግባት ችለዋል” ብለዋል። ይህ መርሃ ግብር ድርጅታቸው የሠራተኛ ኃይል ፍላጎቱን በሰለጠነ ሰው እንዲተካ እንደረዳውም ገልፀዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ስፔሻሊስት አቶ ፍቅረስላሴ ንጉሴ እንደገለጹት፣ በክፍለ ከተማ አስተዳደሩ ስር በሦስተኛው ዙር ብቻ 1 ሺህ 113 ወጣቶች በተለያዩ 135 ድርጅቶች ውስጥ ልምምድ አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ 60 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በእያንዳንዱ ዙር ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶችን በቋሚነት ወደ ሥራ ማሰማራት ተችሏል።
አቶ ፍቅረስላሴ አያይዘውም፤ “የሥራ ላይ ልምምድ ለሚያደርጉ ወጣቶች እንደተቋም የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸዋል፡፡ ድጋፍና ክትትሉ በተቋሙ ብቻም ሳይሆን ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም ሕዝቡ በቀጥታ የሚሳተፍበት ነው፡፡ የድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎችም ሚና ከፍተኛ ነው” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን፣ የዓለም ባንክ ለዚህ ፕሮጀክት እያደረገ ያለውን የበጀት ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ያደንቃሉ። ይህ ፕሮጀክት ከ2014 እስከ 2018 በጀት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 49 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ በማስታወስ፤ “የዓለም ባንክ ፕሮጀክት የመጨረሻ ምዕራፍ በሆነው በሦስተኛው ዙር የተሳተፉ 8 ሺህ 852 ወጣቶች የስድስት ወራት ቆይታቸውን አጠናቅቀዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ይፋዊ የምረቃ ሥነ ስርዓቱም በከተማ አቀፍ ደረጃ የፊታችን ማክሰኞ፣ መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከናወናል” ብለዋል።
በተጨማሪም፤ መንግስት የመርሃ ግብሩን ውጤታማነት በማየት፣ በመንግስት ሙሉ ወጪ የሚከናወን 4ኛ ዙር የፓይለት ፕሮግራም በ115 ሚሊዮን ብር በጀት፣ በተመረጡ 20 ወረዳዎች፣ 3 ሺህ ወጣቶችን በመያዝ መጀመሩን ገልጸዋል። ይህ ተግባር እንደ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሥራ አጥነት ቁጥርን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችል ቁልፍ መሣሪያ መሆኑ ታምኖበታል። የ“ብቃት” መርሃ ግብር ወጣቶች ሙያዊ ክህሎትና የሥራ ሥነ- ምግባር እንዲላበሱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። ወጣቶቹም ከጥገኝነት ወጥተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚረዱበት፣ አልፎም የራሳቸውን ሥራ የሚፈጥሩበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል። ስለሆነም፤ እንዲህ ዓይነቱን በቅንጅትና በትብብር ዕውን የሚሆን ፍሬያማ የተግባር እንቅስቃሴ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል እንላለን፡፡
በደረጀ ታደሰ