AMN – መጋቢት 11/2018 ዓ.ም
1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በአዲስ አበባ ስታዲየም በታላቅ መንፈሳዊ ድባብ ተከብሯል።
የዘንድሮው በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱ ባለፈ፣ በከተማዋ የተከናወኑ አዳዲስ የልማት ሥራዎች ለበዓሉ አከባበር በፈጠሩት ምቹ ሁኔታና በሰጡት ውበት ልዩ ገጽታ ተላብሶ ውሏል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የታደሙ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን እንደገለጹት፤ የከተማዋ አዲስ መልክ ለሶላት ሥነ-ሥርዓቱ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ የነዋሪውን መንፈስ የሚያድስ ሆኗል።

የሃይማኖት አባት የሆኑት ኡስታዝ ከድር ለገሰ በሰጡት አስተያየት፣ መንገዶች ሰፍተውና አምረው ለሶላት ምቹ መሆናቸው በዓሉን በነፃነትና በደስታ ለማክበር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
በተለይም ከስታዲየም ዙሪያ እስከ ፒያሳ ያለው የመንገድ ውበት ምዕመኑ በተዝናኖት ስሜት ሶላቱን እንዲያከናውን ማድረጉን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
አቶ አብዱ መሃመድ የተባሉ የሃይማኖት አባት በበኩላቸው የከተማዋ የልማት ሥራዎችና አዲስ መልክ ከውበት ባለፈ የሰውን አመለካከትና አኗኗር ጭምር የሚቀይሩ መሆናቸውን በመጥቀስ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው፣ የረመዳን ወር ምዕመናን ወደ ፈጣሪያቸው በአምልኮ የሚመለሱበትና መልካም ተግባራትን የሚያበዙበት የተቀደሰ ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል።
ወሩ ምስኪኖች የሚረዱበት፣ የተራቡ ወገኖች የሚጎበኙበትና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ የፍቅርና የመረዳዳት ትምህርት የተገኘበት መሆኑንም አክለዋል።

በተመሳሳይ ኡስታዝ ካሚል ጣሀ በሰጡት ማብራሪያ፣ ረመዳን በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ የመቻቻል፣ የእዝነት እና የስነ-ምግባር ለውጥ የሚታይበት ልዩ ወር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ አስተያየት ሰጪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በረመዳን ወር የተለማመድናቸው እንደ ምስኪኖችን መርዳት፣ እርስ በእርስ መረዳዳት፣ የቂም በቀል መፋቅ እና መቻቻል ያሉ መልካም እሴቶች በቋሚ የሕይወት ጉዟችን ውስጥ በተግባር ሊተረጎሙ ይገባል ብለዋል።
በበረከት ጌታቸው