AMN – መጋቢት 12/2018 ዓ.ም
ሚዲያዎች ለብሔራዊ ጥቅም የመቆም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለ21 ቀናት በልዩ የትኩረት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 36 የሚዲያ ባለሙያዎችን አስመረቀ።
በምረቃ ስነ-ስርአቱ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሚዲያዎች የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግስት ለሚዲያ ተቋማትና ለባለሙያዎች ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሃይማኖት ዘለቀ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃንና ባለሙያዎች በየጊዜው ራሳቸውን በዕውቀት በማበልጸግና በማነጽ አገራዊ ተልዕኳቸውን በታማኝነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚዲያ ተቋማትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራውን ጎን ለጎን፣ የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ሃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም የሚዲያ ባለሙያዎች የሚሰሯቸው ዘገባዎች በዕውቀትና በፈጠራ የተደገፉ፣ ግልጽነት ያላቸውና የአገርን የረጅም ጊዜ ጥቅም ያስጠበቁ ሊሆኑ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ አስገንዝበዋል።
ስልጠናው በዋናነት የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተመራቂ ባለሙያዎች ካለው ዓለም አቀፋዊ የመረጃ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን በማስማማት ለሕዝብ ጥቅም እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመሀመድ ቶፊቅ
