ሪያል ማድሪድ ከ አትሌቲኮ ማድሪድ

You are currently viewing ሪያል ማድሪድ ከ አትሌቲኮ ማድሪድ

AMN- መጋቢት 13/2018 ዓ.ም

የስፔን ላሊጋ ለኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት ታላቁን ደርቢ ያስተናግዳል።

ሪያል ማድሪድ ከ አትሌቲኮ ማድሪድ የሚያከናውኑት የማድሪድ ደርቢ ምሽት 5 ሰዓት በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ይደረጋል። በአልቫሮ አርቤሎዋ የሚመራው ሪያል ማድሪድ ወደ ጥሩ ብቃቱ ተመልሷል። በተለይ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ማንችስተር ሲቲን በደርሶ መልስ ማሸነፉ የቡድኑን በራስ መተማመን ከፍ አድርጎታል።

አትሌቲኮ ማድሪድም ምንም እንኳን በመልሱ ጨዋታ 3ለ2 ቢሸነፍም ቶተንሃም ሆትስፐርስን በድምር ውጤት 7ለ5 በመርታት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።

ሁለቱ ታሪካዊ ተቀናቃኞች ዘንድሮ በሁለት አጋጣሚ ተገናኝተው አንድ አንድ ድል አስመዝግበዋል። በላሊጋው የመጀመሪያ ዙር አትሌቲኮ በዣቪ አሎንሶ ይመራ የነበረው ማድሪድን 5ለ2 አሸንፎ ጣፋጭ ድል ማግኘቱ ይታወሳል። ማድሪድ በአንፃሩ በስፔን ሱፐር ካፕ 2ለ1 በማሸነፍ አትሌቲኮን ከውድድሩ ውጪ አድርጎ ነበር።

ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና ጋር ያለውን የአራት ነጥብ ልዩነት የበለጠ እንዳይሰፋ ለማድረግ የበላይነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። ከዋንጫ ፉክክሩ የራቀው የዲያጎ ሲሞኔው አትሌቲኮ ማድሪድ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ የሚያስገኝለትን ደረጃ አስተማማኝ ለማድረግ ውጤቱ ያስፈልጋል።

አትሌቲኮ በቅርብ ዓመታት የጎረቤቱ ክለብ ላይ የበላይነት ወስዷል። በመጨረሻ ስድስት የላሊጋ ጨዋታዎች በሪያል ማድሪድ አልተሸነፈም። ባለፉት ሦስት ዓመታት በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ የተደረጉ የማድሪድ ደርቢ የላሊጋ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 1ለ1 ነው የተጠናቀቁት።

በዛሬው ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ወሳኝ ግብ ጠባቂው ቲቦ ኩርቷን በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም። አጥቂው ኪሊያን ምባፔ ግን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review