አዲስ አበባ ከመተላለፊያ ማዕከልነት ወደ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻነት

You are currently viewing አዲስ አበባ ከመተላለፊያ ማዕከልነት ወደ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻነት

AMN- መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ድርጅት ቱሪዝም ለአንድ ሀገር እድገት የለውጥ ሞተር እና የዘላቂ ልማት መሳሪያ እንደሆነ ይገልፃል። ድርጅቱ ቱሪዝምን ከዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማያያዝ፣ ድህነትን ለመቀነስና ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን ለማምጣት እንደ ትልቅ ማነቃቂያ ይመለከተዋል።

ቱሪዝም ለአገራት ትልቅ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለመሸፈን እንደሚረዳ ያብራራል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቱሪዝም ከዓለም የኢኮኖሚ ምርት 10% ያህሉን እንደሚሸፍንና ይህም ለአገራት የኢኮኖሚ ጥንካሬ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይገልፃል።

ቱሪዝም በዓለም ላይ ካሉ 10 ዋና ዋና የሥራ ዕድሎች ውስጥ አንዱ መሆኑን የሚገልጸው ድርጅቱ፣ በተለይ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲስፋፉ የሚያደርግ ዘርፍ እንደሆነም ያስረዳል፡፡የኢትዮጵያ መንግስትም ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝም አንዱ እንዲሆን በማድረግ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

አንድ ሀገር ወይም ከተማ በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ድርጅት የተቀመጡትን አምስቱን መስፈርቶች ማለትም ማራኪና አዳዲስ መስህቦች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያዎች፣ መሰረተ ልማትና አገልግሎቶች፣ ተደራሽነት እና ተግባራት ማሟላት ይጠበቅበታል።

በዚህም መሰረት የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ለቱሪስት ተመራጭ መዳረሻ ለመሆን እነዚህን መስፈርቶች እያሟላች ትገኛለች።

ከተማዋ ብሔራዊ ሙዚየምን ጨምሮ፣ በቅርቡ የተገነቡትን እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የአንድነት ፓርክ ያሉ ግዙፍ መስህቦችን አካትታለች።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከተማዋን የታሪክና የዘመናዊነት ጥምረት ያካተተች የቱሪስት መስህብ እንድትሆን አድርገዋታል።

በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተማዋን ከዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ የሚጫወተው ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለእግረኛ ተጓዦችና ለጎብኚዎች ምቹ የሆኑ መንገዶችን በመፍጠር የከተማዋን የውስጥ እንቅስቃሴ በእጅጉ አሻሽሎታል።

አዲስ አበባ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ያላትን የበላይነት ለማስቀጠል እንደ ስካይላይት ያሉ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ምቹ የእንግዳ ማረፊያዎችን በማስፋፋት የጎብኚዎችን ማረፊያ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እያሟላች ትገኛለች።

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች፣ የከተማ ጽዳትና የፓርክ አገልግሎቶች መስፋፋት ቱሪስቶች በከተማዋ ቆይታቸው ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በተጨማሪም እንደ መስቀል፣ ጥምቀት እና ኢሬቻ ያሉ ደማቅ በዓላት፣ የባህል ምግቦችና የምሽት መዝናኛዎች ለቱሪስቶች ልዩ ትዝታን የሚፈጥሩ ተግባራት ሆነዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ በኢኮኖሚው ላይም አወንታዊ መነቃቃትን ፈጥሯል።

እነዚህ እና ሌሎችም ተግባራት የአዲስ አበባ ከተማ ከመተላለፊያ ማዕከልነት ባለፈ ለጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ እየሆነች ስለመምጣቷ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review