AMN- መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተአማኒ፣ ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የጸጥታ ኃይሎች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና የፌዴራል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት በምርጫ ሰላማዊነት ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ እየተካሔደ ይገኛል።
ስልጠናው በዋናነት እየተሰጠ ያለው ከየክልሉ ለተወጣጡ የፖሊስ አባለት ሲሆን፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተአማኒና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስን ሚና ማላቅን ትኩረቱ አድርጓል።
ምርጫ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት በምልዓት የሚገለጥበት፣ የፖለቲካ የውድድር መድረክ ነው ያሉት የኢትየጵያ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ፍጹም ፍትሐዊ፣ተአማኒና ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ሚና አይተኬ ነው ብለዋል።
ፖሊስ ገለልተኛነቱንና ሙያዊነትን በማስቀደምና የመራጮችንና የተመራጮችን መብት በማስጠበቅ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት ብለዋል።

ይህንን ትልቅ መድረክ ለተለያዩ ዓላማዎች ለማዋል የሚጥሩ አካላትን በመቆጣጠርና ህግን በማስከበር እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ንበረቶችን መጠበቅ ተቀዳሚ ሥራዎች መሆናቸውንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ታምራት ሙሉጌታ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ ፖሊስ እሴቱን ባከበረ መልኩ ይሰራል ብለዋል።
ፖሊስ ለሀገሩና ለዜጋው ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ብዝሀነትን አክብሮ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በመጠበቅና በማክበር ሁነቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በሄኖክ ዘነበ