AMN – መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
የአፋር ክልል በታሪክና በተፈጥሮ ሀብት የታደለ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የተገነባውን ዘመናዊውን “ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ” መርቀው በይፋ ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የአፋር ሕዝብ ሀገሩን የሚወድ፣ ብርቱና ትጉህ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህ ሕዝብ መሰል የልማት ሥራዎችን ማከናወንና የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለልማት ማዋል ለመንግሥት ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኘውንና በአንድ አካባቢ ተከማችቶ የሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ የተፈጥሮ የዘንባባ ጫካ የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲህ ያለ ልዩ ተፈጥሯዊ ስጦታ ማግኘት እምብዛም ያልተለመደ መሆኑን አስረድተዋል።
አካባቢው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት መልማት የነበረበት ቢሆንም፣ አሁን የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የጠፋውን ጊዜ ለማካካስ በትጋት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዕድል ያንቀላፉ ሰዎችን አትቀስቅስም” የሚለውን የአፋር ብሂል በመጥቀስ፣ ክልሉ ገና ያልተነኩ በርካታ የልማት ዕድሎች ያሉት በመሆኑ ሳይዘናጉ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል፣ በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ ባሉ ዓለም አቀፍ የግብርና ግብዓቶች ላይ መስተጓጎል መፈጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ይህንን ዓለም አቀፋዊ ጫና ለመቋቋም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ያሉትን የዝናብ አማራጮች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም በበልግ ወቅት ቢያንስ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ከተቻለ የተፈጠረውን ችግር መሻገር እንደሚቻል ጠቁመው፣ አርሶ አደሩ ሳይሰለች ካረሰና ወቅቱን ጠብቆ ከተንቀሳቀሰ በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ የሚታየው መከራ ሳይሆን ጥጋብ እንደሚሆን አፅንዖት ሰጥተዋል።
በአጠቃላይ በአፋር ክልል የተከናወነው ይህ የልማት ሥራ ለቱሪዝም ዕድገትና ለግብርናው ዘርፍ መነቃቃት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ በላቀ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አቅም እንዳለው ተመላክቷል።
በበረከት ጌታቸው