የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በትራፊክ ደህንነት ላይ አዳዲስ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታወቀ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በትራፊክ ደህንነት ላይ አዳዲስ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታወቀ

AMN – መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በከተማዋ ያለውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ይበልጥ ምቹ፣ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ባለሥልጣኑ ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስም በሞተር ብስክሌቶች ላይ የጂፒኤስ (GPS) መሣሪያ እንዲገጠም፣ አሽከርካሪዎች የመንቀሳቀሻ ፈቃድ እንዲይዙና የትራፊክ ሕግጋትን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ይገኛል።

የባለሥልጣኑ የቁጥጥርና ደንብ ማስከበር ዳይሬክቶሬት የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ኃይማኖት አዳነ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ9,000 በላይ በሚሆኑ የሞተር ብስክሌቶች ላይ የጂፒኤስ መሣሪያ ተገጥሟል።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በማኅበርም ሆነ በግል አገልግሎት የሚሰጡ ማንኛውም የሞተር አሽከርካሪዎች፣ ከባለሥልጣኑ በተሰጣቸው የመንቀሳቀሻ ፈቃድ መሠረት መሣሪያውን በሞተራቸው ላይ የማስገጠም ግዴታ እንዳለባቸው ተመላክቷል።

የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ መተግበሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ በተለይም ለባለንብረቶች የንብረት ጥበቃን ለማረጋገጥ፣ ለአሽከርካሪዎች ደህንነት፣ ወንጀልን ለመከላከልና ሕጋዊ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት ትልቅ ሚና ይጫወታል።

በተጨማሪም አሠራሩ በሞተረኞች እንቅስቃሴ ላይ ግልጽነትን በመፍጠር የደንበኞችን እምነት ለመጨመርና የሕግ ተፈጻሚነትን ለማጠናከር እንደሚረዳ አቶ ኃይማኖት አብራርተዋል።

በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የሞተር ላይ ስርቆቶችና ሌሎች ወንጀሎች መቀነሳቸው ተገልጿል።

ባለሥልጣኑ አውቶማቲክ የሕግ ማስከበርና የፓርኪንግ ማኔጅመንት ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ በትራፊክ ሕግ ጥሰቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም መሠረት በተያዘው በጀት ዓመት የጭንቅላት መከላከያ (ሄልሜት) ሳያደርጉ፣ ታርጋ ሳይኖራቸው፣ ጂፒኤስ ሳይገጥሙና የመንዳት ፈቃድ ሳይኖራቸው የተገኙ 120 ሞተረኞች ላይ የቅጣት እርምጃ ተወስዷል።

አዲሱ እርምጃ በትራፊክ ደህንነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የተገመተ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ሕግን በማክበር ለደህንነቱ መጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review