AMN – መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለትውልድ መርሃ ግብር እየተሰሩ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እያዳረሱ ይገኛሉ።
ሰፊ ተፈጥሯዊ ፀጋ እና ሐብት እያላቸው ተዘንግተው የቆዩ አካባቢዎችን የልማት ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውም በተግባር ተገልጧል።
በየአካባቢው ያለውን ተፈጥሮአዊ ሐብት ከግምት በማስገባት እየተገነቡ ያሉት የቱሪዝም ፕሮጀክቶች በየክልሎቹ የተደበቁ ውበቶችንና የልማት አቅሞችን ፈልፍለው እያወጡ ይገኛሉ።
ደንዲ ኢኮ-ሎጅ ፣ ሸበሌ ሪዞርት ፣ ገርዓልታ ፣ ሎጎ ሐይቅ ገርባ ዳራ ና ኒዒን ሌ ፓልም ሎጆች ተፈጥሮን በመግለጥ በዘመናዊ መልኩ የተሰሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ናቸው። እነኚህ ፕሮጀክቶች ቀደም ሲል መስል ግንባታዎች ተካሂዶባቸው የማይታወቁ ክልሎች ያላቸውን እምቅ አቅም ያሳዩ ናቸው።
ከወራት በፊት የተመረቀው በሶማሌ ክልል የሚገኘው የሸበሌ ሪዞርት እና ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመረቁት በአፋር ክልል የተገነባው ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ አይን ገላጭ ፕሮጀክቶች የልማት አካታችነት ማረጋገጫ ይሆናሉ።
ከገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ዋነኛው የሆነውና በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሸበሌ ሪዞርት ፣ በይዞታው 10ሺ የፍራፍሬ ተክሎች ካረፉበት የፍራፍሬ ፓርክ ጀምሮ እስከ ዋናው የግመል ፓርክ ድረስ የተሰራበት መንገድ እያንዳንዱ የሪዞርቱ ገጽታ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሐብት የሚያንፀባርቅ ሆኖ ነው።
የአፋር ክልሉ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ በተለያዩ የፍራፍሬ እና የደን ዛፎች በለመለመ 78,000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈ ነው። ፍልውሃ መዋኛ ፣ ሁለት ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቆች እና 3.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግር ጉዞ ምቹ መንገድን አካቷል።

የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ታሪካዊ እጥፋት ያመጡ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ ህልምን ወደ እውነት የመለወጥ፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮና የባህል ጸጋዎች መላው ዓለም የሚካፈለው ቅርስ በማድረግ የመደመር መንፈስ በተግባር ታይቶባቸዋል።
ከሶማሊ ዋቢ ሸበሌ ዳርቻ እስከ ቤንች ማጂ ደንዲ ኢኮሎጅ ፣ ከወሎ ሎጎ ሐይቅ እስከ አፋር ፍልውኃዎች ላይ የተሰሩት ፕሮጀክቶች ለየአካባቢው ኢኮኖሚ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥሩ ለነገው ትውልድ የሚሻገሩ የዕድገት መሰረት ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሎጁን በመረቁበት ወቅት “መሰራት የነበረበት የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ነበር ፤ አሁን ስለዘገየን አንቆጭም። ነገር ግን ይህንን ስለሰራን ደግሞ አንረካም፣ ሩጫችን ገና ብዙ እንደሆነ፣ አፋር ገና እንዳልተነካ አስበን ይህንን ጅማሮ ይበልጥ በማላቅ ለማስቀጠል እንተጋለን ሲሉ ገልፀዋል።
በታደሰ ሽፈራው