የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ እና የዓለም የነዳጅ ፖለቲካ

You are currently viewing የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ እና የዓለም የነዳጅ ፖለቲካ

AMN- መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ወቅታዊ ውጥረት እና ጦርነት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህንን ተከትሎ የዓለም ሀገራት እንደየጥቅማቸው እና እንደየጂኦ-ፖለቲካዊ አሰላለፋቸው የተለያዩ እርምጃዎችንና አቋሞችን እየወሰዱ ይገኛሉ።

የበለፀጉ ሀገራት በተለይም የዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኤጀንሲ አባላት፣ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይንር ለመከላከል የራሳቸውን የነዳጅ ክምችት ወደ ገበያ ለማውጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ይገለፃል።

ይህም በጦርነቱ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የአቅርቦት መቋረጥ ለማካካስ ታስቦ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ አሜሪካ ዋጋን ለማረጋጋት የስትራቴጂክ ክምችቷን በየጊዜው የመጠቀም ዝንባሌ እንደምታሳይ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ጦርነቱ በነዳጅ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን የሚያስከተለውን የደህንነት ስጋት ለብዙ ሀገራት ዳግም ያስገነዘበ እና የማንቂያ ደወል ተደረጎ ተወስዷል ።

ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የተማሩት የአውሮፓ ሀገራት፣ አሁን ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ወደ ፀሐይ፣ ንፋስ እና ሃይድሮጅን ኃይል የሚደረገውን ሽግግር እያፋጠኑ መሆኑ ተነግሯል። ሀገራት ከውጭ በሚመጣ ነዳጅ ከመታወክ ይልቅ የራሳቸውን የውስጥ ኃይል አማራጭ ማሳደግ እንደ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ እየተመለከቱትም ይገኛል።

በሌለ በኩል ሀገራት ነዳጅ የሚገዙባቸውን ቀጣናዎች የመቀያየር ሥራ እየሠሩ ሲሆን፣ ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ይልቅ ከአፍሪካ ወደ ናይጄሪያ እና አንጎላ፣ ከላቲን አሜሪካ ወደ ብራዚል እና ጉያና እንዲሁም ወደ ሰሜን አሜሪካ ምርቶች ፊታቸውን እያዞሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ህንድ እና ቻይና ደግሞ አሁንም በቅናሽ የሚገኘውን የሩሲያ ነዳጅ በመግዛትና ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማመጣጠን በብልሃት እየሄዱ ይገኛሉ።

ብዙ የአፍሪካ መንግስታት የነዳጅ ዋጋን ለመቆጣጠር ሲጠቀሙበት የነበረውን ድጎማ ለመቀነስ ወይም ሙሉ በሙሉ ለማንሳት እየተገደዱ መሆኑም ተነግሯል።

የዚህ ምክንያትም የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር መንግስታት ድጎማውን ለመሸፈን የሚያወጡት ወጪ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ነው። ይህ እርምጃ በሀገር ውስጥ የትራንስፖርት እና የምግብ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ንረት እያስከተለ እንደሚገኝም መረጃዎች ያመላክታሉ።

እንደ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ሊቢያ እና አልጄሪያ ያሉ ሀገራት ይህንን አጋጣሚ የውጭ ምንዛሬ ገቢያቸውን ለማሳደግ እየተጠቀሙበት እንደሆነም ይገለፃል። ናይጄሪያ በቅርቡ ሥራ የጀመረውን የዳንጎቴ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ በመጠቀም የነዳጅ ምርትን በሀገር ውስጥ ለማጣራትና ወደ ውጭ ለመላክ እየጣረች መሆኑም ተገልጿል።

የአውሮፓ ሀገራት ከሩሲያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የሚያገኙትን ነዳጅ በአፍሪካ ምርቶች ለመተካት ፍላጎት በማሳየታቸው፣ የአፍሪካ አምራቾች ምርታቸውን ለመጨመር ኢንቨስትመንት እያሳደጉ መሆኑም ተነግሯል።

ነዳጅ የማያመርቱ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሞሮኮ ያሉ ሀገራት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት የጀመሩትን የታዳሽ ኃይል ጉዞ እያፋጠኑ መሆኑም እየተገለጸ ይገኛል። ኢትዮጵያ የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በማበረታታት ቀዳሚ እርምጃ ወስዳለች። ኬንያ በጂኦ-ተርማል፣ ሞሮኮ ደግሞ በፀሐይ ኃይል ላይ ትኩረት በማድረግ በነዳጅ ላይ የተመሰረተውን የሃይል ፍላጎታቸውን ለመቀነስ እየሰሩ ነው።

የአፍሪካ ሀገራት የነዳጅ አቅርቦት ስጋትን በጋራ ለመቋቋም ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ፋይናንሺያል ታይምስን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review