“መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ብሔራዊ ጥቅም ግን የጋራ ህልውናችን ነው” – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

You are currently viewing “መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ብሔራዊ ጥቅም ግን የጋራ ህልውናችን ነው” – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

AMN — መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል እንዲሁም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ብሔራዊ ጥቅም የአንድን ፓርቲ ወይም የጊዜያዊ መንግሥትን ቅቡልነት ማጉላት ሳይሆን፣ ሀገርን ለማስቀጠል የሚደረግ የጋራ ጥረትና የህልውና መሠረት መሆኑን ገለጹ።

አምባሳደር ሬድዋን ጋዜጠኞች ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ መርሆዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ ብሔራዊ ጥቅም የሁሉንም መንግሥታት ጥረት ደምሮ፣ ከስህተቶች እየተማሩና ስኬቶችን እያጎለበቱ ሀገርን ከፍ የሚያደርጉበት ሂደት መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ መንግሥታት በየወቅቱ በሥርዓት ሊተካኩ ቢችሉም፣ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ግን የማይለወጥና የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ የሚሻ የጋራ ዓላማ ነው ብለዋል።

“ብሔራዊ ጥቅም የሁላችንም ጥቅም ነው” ያሉት አምባሳደሩ፤ ጽንሰ-ሐሳቡ በሀገር ህልውና፣ በእድገትና በጠንካራ ክንድ ላይ እንደሚቃኝ አስረድተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን አክለውም፣ በብሔራዊ ጥቅም ላይ መሥራት ማለት በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት “ማንቆለጳጰስ” ወይም የአንድ ፓርቲ ተከታይ መሆን አለመሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

ይልቁንም መንግሥትን በማረም ረገድ የሚኬደው ርቀት ማኅበረሰቡን ወደ የጋራ ጥበብ እንደሚያሸጋግረውና ይህም ለሀገር ጥንካሬ መሠረት እንደሚሆን አስረድተዋል።

ሀገር ስትከበርና ስትታወቅ ዜጎቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንደሚያገኙ የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ ለሀገር የጋራ ቅቡልነት መሥራት በራስ ላይ እንደሚደረግ ኢንቨስትመንት ሊቆጠር እንደሚገባ መክረዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review