ዓለም አቀፉን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ ሐገራት ምን የመፍትሔ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው?

You are currently viewing ዓለም አቀፉን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ ሐገራት ምን የመፍትሔ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው?

AMN- መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት በስከትለው ዓለም አቀፍ የነዳጅ እጥረት ሳቢያ ሀገራት የአጭርና የረጅም ጊዜ ርምጃዎችን እንዲወስዱ አስገድዷል።

ሀገራት የተለያዩ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን እየወስዱና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎቻቸውንም እያሻሻሉ ይገኛሉ።

እንደ ዘቢዝነስ ስታንዳርድ (tbsnews.net) ዘገባ አስቸኳይ የኃይል ቆጠባ እርምጃዎች ፣ የአቅርቦት አስተዳደር እና ክምችት፣ ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች ፣ የረጅም ጊዜ መዋቅራዊ ለውጦች እና የመሳሰሉት ሀገራት እየወሰዱዋቸው ካሉ የመፍተሄ ርምጃዎች ተጠቃሾች ናቸው። እንደ ፓኪስታን ፣ ሲሪላንካ፣ ታይላንድ… ወዘተ ያሉ ሐገራት አስቸኳይ የኃይል ቁጠባ እርምጃዎች እየወሰዱ ካሉት ተጠቃሾች ናቸው።

ስሪላንካ በዲጂታል (QR code) የታገዘ የነዳጅ ክፍፍል ስርአት ስትዘረጋ፣ ምያንማር ደግሞ በታርጋ ቁጥር መለየት (ጎዶሎ/ሙሉ ቁጥር) የመኪና እንቅስቃሴን ገድባለች።

ፓኪስታን እና ፊሊፒንስ የሥራ ቀናትን ወደ አራት ዝቅ ሲያደርጉ፣ ባንግላዴሽ የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ ትምህርት በኢንተርኔት እንዲሆን አድርጋለች።ታይላንድ የመንግሥት ሠራተኞች ከቤት እንዲሠሩና የአየር ማቀዝቀዣዎች ከ26-27 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳያልፉ አዝዛለች።

ስትራቴጂካዊ ክምችትን መልቀቅ ፣ ወደ ውጭ የሚላክ ነዳጅን መገደብ ፣ አዳዲስ የግዢ ስምምነቶች የመፈፀም ስልቶችን የተከተሉ ሐገራትም አሉ። አውስትራሊያ እና ደቡብ ኮሪያ ገበያውን ለማረጋጋት በሚሊዮን የሚቆጠር ሊትር ነዳጅ ከክምችታቸው ወደ ገበያ አውጥተዋል።

ቻይና የነዳጅ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ስታቆም፣ ማሌዥያም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች ነው።እንደ ህንድ እና ስሪላንካ ያሉ ሀገራት ከአማራጭ ምንጮች እንደ ሩሲያ ካሉ ሐገራት ነዳጅ ለማስገባት እየጣሩ ነው።

አንዳንድ ሐገራት ድጎማና የታክስ ቅነሳ እና ትርፍን መቆጣጠር የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች እያደረጉ ይገኛሉ። ጣሊያን እና ፈረንሳይ የነዳጅ ኩባንያዎች ካልተገባ ትርፍ ላይ ግብር እንደሚጥሉና ማደያዎችን እንደሚቆጣጠሩ አስታውቀዋል።

ወደ ታዳሽ ኃይል መሸጋገር የረጅም ጊዜ መዋቅራዊ ለውጦች እያደረጉ ያሉ ሐገራትም አሉ። ቀውሱ አውሮፓ ከቅሪተ አካል ነዳጅ ወጥታ ወደ ንጹህ ኃይል የምታደርገውን ጉዞ አፋጥኖታል። ህንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን (EV) በስፋት እያስተዋወቀች ነው። ሀገራት በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ያለባቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ አማራጭ የኃይል ምንጮችን በንቃት እየፈለጉ ነው።

በኢትዮጵያም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ የተለያዩ ነዳጅ ቆጣቢ አማራጮችን (የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት መጠቀም፣ ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም…ወዘተ) ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review