AMN- መጋቢት 15/2018 ዓ.ም
ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ቀጥላለች፤ የትራምፕን የድርድር ንግግርም “የፈጠራ ወሬ” ስትል አጣጥላለች።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኃይል መሠረተ ልማት ለመደብደብ የነበራቸውን እቅድ ለጊዜው ማዘግየታቸውን ቢገልጹም፣ ኢራን ግን በርካታ ሚሳይሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች። በቴል አቪቭ እና በሰሜን እስራኤል የሚሳኤል መከላከያ ድምጾችና ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን ባለስልጣናት ጋር “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ” ውይይት ማድረጋቸውንና ለሰላም ስምምነት መቃረባቸውን ቢገልጹም፣ የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባቂር ቃሊባፍ ግን ይህንን አስተባብለዋል። “ምንም ዓይነት ድርድር አልተደረገም፤ ትራምፕ የነዳጅ ገበያን ለመቆጣጠር የፈጠራ ወሬ እየተጠቀሙ ነው” ብለዋል።
የትራምፕ መግለጫ መጀመሪያ ላይ የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ቢያደርግም፣ የኢራን ማስተባበያ ግን ገበያውን በድጋሚ ስጋት ላይ ጥሎታል። የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ4.2 በመቶ ጨምሮ በበርሜል 104 ዶላር ደርሷል። ኢራን ከዓለም የነዳጅ ዝውውር 20 በመቶ የሚሸፍነውን የሆርሙዝ ሰርጥ በመዝጋቷ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ስጋት ተፈጥሯል።

ምንም እንኳን ኢራን ድርድር የለም ብትልም፣ የፓኪስታን ባለስልጣናት ግን በዚህ ሳምንት በኢስላማባድ ውስጥ የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ሊገናኙ እንደሚችሉ እየገለጹ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል። ጦርነቱ ከተጀመረበት ከፈረንጆቹ የካቲት 28 ጀምሮ እስከ አሁን ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ነው የተዘገበው።
ቀጣናው አሁንም በማንኛውም ሰዓት ሊፈነዳ በሚችል ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይገኛል።
በታምራት ቢሻው