ከንቲባ አዳነች አቤቤ 3ኛውን የ‘አዲስ መሶብ’ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ሥራ አስጀመሩ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ 3ኛውን የ‘አዲስ መሶብ’ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ሥራ አስጀመሩ

AMN መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በከተማችን 3ኛውን የ‘አዲስ መሶብ’ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ሥራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ሥራ የጀመረው ይህ ባለ ሰባት ወለል ዘመናዊ ማዕከል፣ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ አቀናጅቶ ጊዜን፣ ወጪን፣ ጉልበትን በመቆጠብ እና እንግልትን በማስቀረት ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ የታለመ መሰረታዊ የለውጥ እርምጃ ነው።

ማዕከሉ የ20 ተቋማትን 112 የተለያዩ አገልግሎቶች በ69 የአገልግሎት መስኮቶች ለተገልጋዮች ያቀርባል። በተጨማሪም 22 ተቋማትን በዲጂታል በይነ-መረብ አስተሳስሯል። ይህም ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ የነበረውን አሠራር በማስቀረት የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃትን፣ ተደራሽነትን እና የዜጎችን እርካታ ከማሻሻሉም ባለፈ፣ ተገልጋዩ ለጉዳዩ የሚያጠፋውን ጊዜ፣ ገንዘብ እና እንግልት በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ለረጅም ዘመን በሙስና እና በዝምድና በተተበተበ ተገቢ ያልሆነ አሠራር ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን የሚሸረሽር እና ላለምነው ሁለንተናዊ ብልፅግና ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም የነዋሪዎቻችንን ጥያቄ በመስማት፣ የአገልግሎት አሰጣጣችንን ወደ ዘመናዊ የዲጂታል አንድ ማእከል አገልግሎት ቀይረናል።

ቀደም ሲል በአራዳ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች ሥራ ያስጀመርናቸው ሁለት ማዕከላት ብቻ ከ120 ሺህ በላይ ደንበኞችን ማስተናገድ መቻላቸው እና ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች በአገልግሎቱ መርካታቸው፣ ለውጡ በተጨባጭ ውጤት የታጀበ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

እስከ መጋቢት መጨረሻ 3 ተጨማሪ፣ እንዲሁም እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ድረስ የማዕከላቱን ቁጥር ወደ 11 በማድረስ ተደራሽነታችንን በከፍተኛ ደረጃ ለማስፋት እየሠራን እንገኛለን።

የአዲስ መሶብ የዲጂታል አንድ ማእከል አገልግሎት ምቹ የስራ ከባቢ የተፈጠረለት ፣ የህፃናት ማቆያ የተሟላለት ፣ በአገልጋይነት መንፈስ በሠለጠኑ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እና በነባር ሠራተኞች ውህደት የሚመራ ነው:: ይህንን ሥራ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ለሰራችሁ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review