በሥራ ሰዓት ስልክ የማይነካበት ቢሮ በአዲስ አበባ እንዳለ ያውቃሉ? እንግዲያውስ እናስተዋውቅዎት

You are currently viewing በሥራ ሰዓት ስልክ የማይነካበት ቢሮ በአዲስ አበባ እንዳለ ያውቃሉ? እንግዲያውስ እናስተዋውቅዎት

AMN – መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

ለመሆኑ ስልክ ሳይዙ ወይንም ሳይነካኩ ለምን ያክል ጊዜ መቆየት ይችላሉ? ሞክረውትስ ያውቁ ይሆን?

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የዜጎችን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ የመንግሰት ተቋማት ላይ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ለካ አንዲህም ይቻላል እያስባሉ ይገኛሉ።

ተቋማትን ለተገልጋይና ለሰራተኛ ምቹ ማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሊጂ የተደገተፈ በማድረግ ብልሹ አሰራርን መከላከልና ቀልጣፋ አሰራርን መተግበር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ነገር ግን ይህም ሆኖ በአብዛኛው ተቋማት የሚሰተዋሉ ለአገልግሎት የመጣን ደምበኛ አስቀምጦ በእጅ ስልክ እና ለሥራ በተፈቀደ ኮምፒዩተር የግል ጉዳይን መፈፀም ባህል እስከመሆን ደርሰው ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ታዲያ ይህንን ልምድ ለማስቀረት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ከተገበራቸው አዳዲስ አሰራሮች መካከል አንዱ ሰራተኞች በስራ ሰዓት የእጅ ስልክ ሳይዙ አገልገሎት አንዲሰጡ ማስቻል ተጠቃሽ ነው።

እንዴት አይሉም ታዲያ

እግር ጥሎዎት ወደ ንግድ ቢሮ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የኦን ላይን አንድ ማዕከል ቢመጡ፣ ስልክ የያዘ ሰራተኛ አያገኙም ሁሉም ሥራቸው ላይ ተጠምደው ተገልጋይን ያስተናግዳሉ።

ምክኒያቱም ሰራተኞች ወደ ቢሮ ሲገቡ ቀድሞ ወደተዘጋጀላቸው ሎከር በመሄድ የእጅ ስልካቸውን እና የያዙትን የግል ቦርሳ ያስቀምጣሉ፣ ከዛም በተቀመጠው የሥራ ሰዓት ያለ ስልክ ንክኪ ሥራዎቻቸውን ይፈፅማሉ።

ሌሊሴ አለማየሁ እና አብዲሳ ለሜቻ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ባለሞያ ናቸው፣ ከዚህ ቀደም ከተገልጋይ ፊት ስልክ እየነካካን የምንሰጠው አገልግሎት ለደንበኛ ምቾት አይሰጥም እኛም ለሥራችን ሙሉ ትኩረት እንዳናደርግ ያደርግ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ያለ ስልክ በሥራ ቦታ እና ሰዓት አለመያዛችን ተገልጋይ ተገቢውን አገልግሎት በሰዓቱ እና በጥራት እንዲያገኝ እንዳስቻለው ነው የተናገሩት።

በቢሮ ከግል የእጅ ስልክ ንክኪ የፀዳ አገልግሎት መሰጠቱ ተገልጋዩ ጉዳዩን በአጭር ጊዜና በተቀመጠው ስታንዳርድ እንዲያገኝ ማስቻሉንና እነዚህ የተቀናጁ የዲጂታል አሰራሮች በቢሮው ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል እና የተገልጋዩም እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ማድረጉ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ተናግረዋል።

እርሶስ በየትኛው የከተማ አስተዳደሩ ቢሮ ለአገልግሎት ተገኝተው ያውቃሉ የታዘቡትን ሃሳብ ያጋሩን ።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review