AMN- መጋቢት 15/2018 ዓ.ም
የሀገር ሀብት ፈሶባቸው መክነው እና ባክነው የቀሩ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ከሞት እያስነሡ ማፋጠን የዚህ መንግሥት ልዩ መለያው ነው፡፡ የመገጭ ግድብ ደግሞ አስረጅ ምስክር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የጎንደርን የውኃ ጥም ይቆርጣል፤ የገበሬውን መሬት ያጠጣል፤ የአካባቢውን ምኅዳር ይለውጣል የተባለው የመገጭ የመጠጥ ውኃ ግድብ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተናል ብለዋል።
እሱ ራሱ የጀመራቸው ብቻ ሳይሆን ተጀምረው የውልደት ስብራት የገጠማቸው ፕሮጀክቶች በብልጽግና መንግሥት አዲስ እስትንፋስ እያገኙ ግንባታቸው እየተፋጠነ መሆኑንም አንስተዋል።
“አቁሞ ያስቀርህ እንደ መገጭ ግድብ” የሚለው ቀርቶ የአካባቢው ሰው “ወድቀህ ተነሣ እንደ መገጭ ግድብ” ብሎ መተረት ጀምሯል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የብልጽግና መንግሥት ብሂል ያስቀይራል ሲሉም አክለዋል፡፡