የወንዝ ዳርቻ ልማት ለበሽታ አጋላጭ ስፍራዎችን ወደ ጤናማነት የመለሰ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የወንዝ ዳርቻ ልማት ለበሽታ አጋላጭ ስፍራዎችን ወደ ጤናማነት የመለሰ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እየለማ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ለበሽታ አጋላጭ የነበሩ አካበቢዎችን ወደ ጤናማነት የመለሰና ፈታኙ ስራ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማን ለማዘመን ስለተሰራው ሥራ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት ከስራዎች ሁሉ ፈታኙ ስራ ቢሆንም ለብዙ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ፣ መጪው ትውልድ የሚኮራበት ልማት መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት 50 ኪ.ሜ. የሚሽፍንና ስምንት ወንዞችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውሃ ቦይ (መፋሰሻ )ብዙ ሀገራት አሳምረው በድንጋይ አድርገው ሰርተው መመልከታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የአዲስ አበባው ግን ለየት ባለ ሁኔታ ከውሃ መሄጃው ግራና ቀኝ እንደየ ቦታው ሁኔታ ከ50 እስከ 100 ሜትር ድረስ የእግረኛ መሄጃ ያለው፣ እጽዋት የተተከሉበት ፣ መዝናኛ ቦታ ያለው እና ለዕይታ በጣም ማራኪ ተደርጎ ተሰርቷል ብለዋል።

እጅግ የቆሸሹና መርዛማ የሆኑትን ወንዞች የማከምና የማጽዳት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያብራሩት።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ ፣ ይብስኑ ለበሽታ የሚያጋልጡ የድህነት መገለጫ እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጥቂት አመታት በኋላ ግን አዲስ አበባ ውስጥ ለመኖር የምንሻማባቸው ቦታዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

​ውሃዎቹን በሚመለከት እየተሰራ ያለው ስራ እንዳላለቀና በተለይ ውሃውን ማጥራት፣ ቆሻሻውን የመለየቱ ስራ ስድስት ሰባት ቦታ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ አብዛኛው ቆሻሻ ውሃ ሲስተም ውስጥ ገብቶ ከታጠበ በኋላ ንጹህ ውሃ መስመሩን ጠብቆ እንዲፈስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review