AMN – መጋቢት 15/2018 ዓ .ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በከተማ፣ በከተሜነት፣ በክትመትና በኮሪደር ልማት ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ስለ ኮሪደር ልማት ምንነት፣ ፋይዳውና አበርክቶው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኮሪደር ልማት በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግቦችን በውስጡ አካቶ የተከናወነ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል። የኮሪደር ልማት የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ያስከተለውን ስራ አጥነት በዘላቂነት የሰበረ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኮሪደር ልማቱ የስራ እድል ብቻ ሳይሆን በርካታ ወጣቶች ክህሎት እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የነዋሪውን መሰረታዊ ፍላጎት ከማሟላቱ በተጨማሪ ለቱሪስት መስህብ በመሆን ከፍተኛ ገቢ እያስገኘ ስለ መሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የኮሪደር ልማቱን በመጀመሪያ አዲስ አበባ ላይ የጀመርነው ከተማዋ የብልጽግና ምልክት በመሆንዋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ከተማ ምልክትም የሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች መተላለፊያ መንገድም ናት ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች አረንጓዴ፣ ንጽህና ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎች እንዲፈጠሩ አስችሏል ብለዋል። አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ አብባለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ስሟ ብቻ ሳሆን መገለጫዋ ሆኗል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የኑሮ ጥራትን በማሻሻል፣ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን ነገር በአካባቢያቸው እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ሳቢና ማራኪ አካባቢ ለመፍጠር አስችሏል ብለዋል።
በመዲናዋ ለተከናወነው የኮሪደር ልማት በአንዳንዶች ዘንድ የተሰጠው ስም ተገቢ እንዳልሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር ) ከዚህ ትምህርት መውሰድ ተገቢ መሆኑንም ገልፀዋል።
በአስማረ መኮንን