“የገጠርን ኑሮ ሳናዘምን ስደትን መግታት አንችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing “የገጠርን ኑሮ ሳናዘምን ስደትን መግታት አንችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሀገሪቱ እየተተገበረ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ታዳጊ ወጣቶች ምቾት ፍለጋ ወደ ከተሞች የሚያደርጉትን ስደት በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የዕለት ተዕለት ሕይወት በሚቀይሩ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማተኮሩንም ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት አርሶ አደሩ በሶላርና በባዮጋዝ የታዳሽ ኃይል አማራጮች እንዲጠቀም በማድረግ፣ እናቶች ለተለያዩ የጤና እክሎች ከሚያጋልጥ የጭስ ብክለት እንዲላቀቁና የአካባቢ ደን እንዳይመነጠር ለማድረግ ያለመ ነው ብልዋል።

በተጨማሪ እንደ ቴሌኮም፣ መብራት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ያሉ ቀደም ሲል በከተሞች ብቻ ተወስነው የነበሩ መሠረተ ልማቶችን በገጠር መንደሮች በማሟላት የከተማን የጥራት ደረጃ ወደ ገጠር ለማውረድ እየተሠራ ይገኛል።

በአካባቢው ከሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡና መኝታ ቤትና ሳሎን የተለየላቸው ሞዴል ቤቶችን በማስፋፋት የነዋሪውን ክብርና ጤና ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ይህ እርምጃ የሰዎች እና የእንስሳት አብሮ የመኖር ኋላቀር ባህል እንዲቀየር በማድረግ የነዋሪውን ጤና ከመጠበቁም በላይ፣ በተለይ ታዳጊ ወጣቶች ምቾት ፍለጋ ወደ ከተሞች የሚያደርጉትን ስደት በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበት እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review