AMN-መጋቢት 15/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥታቸው ለከተሞችና ለከተማ ነዋሪዎች የሰጠውን አዲስ መዋቅራዊ እይታ አስመልክቶ ከቃና ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ ከተሞች የሀገር ስልጣኔ የሚለካባቸው መስታውቶችና የብልፅግና ዋና ሞተር ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።
ቀደምት መንግሥታት ከተማን እንደ ሥጋት፣ ነዋሪውን እንደ ወላዋይ በመፈረጅ የማግለል ዝንባሌ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ከተሞች የሀገር ሀብት የሚመነጭባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ብቻቸውን የሀገሪቱን ግማሽ ያህል የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) የሚሸፍኑ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
አክለውም ከተሞች የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ፍላጎቶች የሚስተናገዱባቸው “የአብሮነት ላቦራቶሪ” መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የከተማ ነዋሪ ለለውጥ ዝግጁና የፈጠራ ባለቤት በመሆኑ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከተሞች የሀገር መኳያና ውበት ከመሆናቸው ባለፈ፣ የዘመናዊነትና የምርታማነት ማዕከል በመሆን እንደ ሀገር “እጅና አእምሮ” ሆነው እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል።
እንደ አዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅማና አዳማ ያሉ ከተሞች እያሳዩት ያለው ፈጣን ዕድገት የመንግሥታቸውን “የመደመር” ፍልስፍናና ለከተሞች የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል ።
በሚካኤል ህሩይ