AMN- መጋቢት 16/07/2018 ዓ.ም
በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ወቅታዊ ቀውስ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታየውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ፣ በሀገራችን ያለውን ውስን ሀብት በቁጠባ መጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ምርታማነት ማሻሻያ እና የልህቀት ማዕከል አስታውቋል።
ችግሩ ተፈትቶ ወደ መደበኛው የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት እስኪመለስ ድረስ፣ እያንዳንዱ ዜጋና ተቋም ያለውን ነዳጅ በኃላፊነት ስሜት ሊጠቀም እንደሚገባ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት በማዕከሉ የአውቶሞቲቭ ስልጠና ዘርፍ ተጠሪ ወ/ሮ ሃይማኖት ዘውዴ ይናገራሉ።
ተቋሙ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ያላቸውን የነዳጅ ፍጆታ የመለካት ሥራ በትኩረት እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም ተቋማቱ በወጣላቸው የነዳጅ ልኬት መሠረት እንዲያወራርዱ በማድረግ አግባብ ያልሆነ የነዳጅ ቅሸባን ለማስቀረትም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሌላው የቴክኒክ ችግር ያለባቸውን ተሽከርካሪዎች የመለየትና የማስተካከል ሥራ መሆኑ ተገልጿል።
ተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት ካጋጠማቸው የነዳጅ ፍጆታቸው ከፍተኛ እንደሚሆን የገለጹት ተጠሪዋ፣ ማዕከሉ ብልሽት ያለባቸውን ተሽከርካሪዎች ወደ ጥገና እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተጠግነው ወደ አገልግሎት መመለስ የማይችሉና አርጅተው ነዳጅ የሚያባክኑ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከገበያና ከሥራ እንዲወገዱ ሙያዊ የውሳኔ ሀሳብ ለሚመለከተው የመንግስትና የግል አካል የማስታወቅ ሥራም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የአሽከርካሪዎችና የኃላፊዎች የክህሎት ማነስ ለነዳጅ ብክነት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን በመግለፅም፣ ማዕከሉ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የቴክኒክና የማሽከርከር ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ ስልጠና አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪን በብቃት በመያዝ የነዳጅ ፍጆታን እንዲቀንሱ ከመርዳቱም ባለፈ፣ ከአያያዝ ጋር ተያይዞ የሚወጡ የጥገና ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚያስቸል ገልጸዋል።
በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል መኖሩ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት በብልሃት ለመወጣትና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ጫናን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

ለነዳጅ እጥረት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ተቋማት ወደ ኤሌክትሪክና የጋዝ ተሽከርካሪዎች እንዲሸጋገሩ ማዕከሉ ሙያዊ የምክር አገልግሎትና የአዋጭነት ጥናት እያቀረበ ይገኛል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለአካባቢ ተስማሚ ከመሆናቸውም ባለፈ በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት የሚቀንሱ በመሆኑ፣ ተቋማት እነዚህን አማራጮች አገልግሎት ላይ እንዲያውሉ ማበረታቻ እየተደረገ እንዳለና ግለሰቦች የብዙኃን ትራንስፖርትን፣ የእግርና የሳይክል ጉዞን እንዲያዘወትሩም ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ከፍተኛ የሞተር አቅም ያላቸውን ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የጉዞ ስልታቸውን በመቀየርና በጋራ በመጓዝ ለቁጠባው ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም አስገንዝበዋል።
በሚካኤል ህሩይ