AMN-መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ ተሞክሮ እየገነባች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ሀገሪቱ የራሷን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯንም ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ከአምስቱ ዋና ዋና የልማት ግቦቿ አንዱ በማድረግና ሁሉንም ዘርፎች የሚያስተሳስር ሥርዓት በመዘርጋት ላይ ትገኛለች።
ቀደም ሲል በአነስተኛ ደረጃ ይገኝ የነበረው የ4G የቴሌኮም መሠረተ ልማት በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ በሆኑ የሀገሪቱ ከተሞች ተደራሽ መሆኑ የዜጎችን የመማር፣ የጤና እና የሥራ ዕድል በማስፋት ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም አብራርተዋል።
ይህንኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማፋጠን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ኢንቨስት የተደረገበት የሳይንስ ሙዚየም እና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገልጿል።

ሀገሪቱ የሰው ኃይልን በቴክኖሎጂ ለማብቃት በጀመረችው የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ሥልጠና እስካሁን 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ገደማ ሰልጣኞች ዕውቅና ማግኘታቸው ኢትዮጵያን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት ሌላው ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የበለጸገው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ከ35 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂውን ለዛምቢያ መንግሥት ለመሸጥ የኮንትራት ስምምነት ተፈርሞ ወደ ሥራ ተገብቷል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ይህ ተሞክሮ ኢትዮጵያ እንደ አየር መንገዱና እንደ መርከብ ድርጅቶቿ ሁሉ በቴክኖሎጂው ዘርፍም በአፍሪካ አህጉር ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ብሎም ቀዳሚነት እንደሚያሳድገውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በሚካኤል ህሩይ