ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ማሳካት በሚያስችል መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ነው

You are currently viewing ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ማሳካት በሚያስችል መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ነው

AMN መጋቢት 16/2018

በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ማሳካት በሚያስችል መልኩ ውጤታማ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ገለጹ።

አስተባባሪው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ዘንድሮ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ የመጀመርያው ምዕራፍ ማጠቃለያ ዓመት በመሆኑ ዝግጅቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም በዘንድሮው መርሃ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ በላይ ለመትከል እቅድ ተይዞ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት የፍራፍሬ ችግኞችን የማስፋት፣ የሀገር በቀል ዝርያዎችን ቁጥር ከፍ የማድረግ ብሎም የእፅዋት አይነት ስብጥር በሰፊው እየተሰራበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በበጋው ወቅት የተከላ ቦታዎችን የመለየት፣ የተለዩ ቦታዎች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የማከናወን፣ ከየአካባቢው አየር ንብረት ጋር የሚጣጣሙ ችግኞችን የማፍላትና የተለዩ ቦታዎች ላይ ካርታ የማዘጋጀት ስራ በስፋት መከናወኑን ነው ያስታወቁት።

በዚህም በክልሎች እስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለችግኝ ተከላ የሚውሉ ቦታዎችን መለየታቸውን ጠቅሰው እስካሁን ከ110 ሺህ በላይ ችግኝ ጣቢያዎች ወደ ስራ ገብተው ችግኞች እያፈሉ ይገኛሉ ብለዋል።

በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ7 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል በእቅድ መያዙን ተናግረው እስካሁን 6 ነጥብ 1 ቢሊየን ችግኝ ዝግጁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በቀሪው ጊዜ የእንክብካቤ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቅሰው ጉድጓድ የማዘጋጀት ስራዎችን ጨምሮ ሌሎችም እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን የክረምት ዝናብ ብቻ የመጠበቅ ልምድ መቀየሩን ጠቁመው ይህም ችግኞች ረጅም የዝናብ ወቅት እንዲያገኙ በማድረግ የፅድቀት መጠናቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምረው አስረድተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አሁን ላይ የህዝቡ ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም የዜጎችን የባለቤትነት ስሜት የማሳደግ እና የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review