AMN — መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ፣ እስካሁን ባከናወንኩት ሥር በመዲናዋ የሚፈፀሙ ጥሰቶችን 83 በመቶ መቀነስ ችያለሁ አለ።
ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከወረዳ እስከ ማዕከል ለሚገኙ አመራሮች ስልጠና ሲጀመር ነው ይህ የተገለፀው።
የአዲስ አበባ ከተማ ዝማኔን የሚመጥን አቅም ግንባታ እየፈጠረ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።
ስልጠናው የአዲስ አበባ ከተማን ፈጣን እድገት የሚመጥን የአመራር ግንባታን ለማከናወን ያለመ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ መዲናዋን የሚመጥን ኦፊሰርና አመራር በመገንባት ተቋማዊ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን እያሳደገ እንደሚገኝም ነው ዋና ስራአስኪያጁ የገለጹት።

በመዲናዋ ደንብ ጥሰትን ለመከላከልና ህግን ለማስከበር በቴክኖሎጂ በመታገዝ ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ሻለቃ ዘሪሁን እነዚህ ቴክኖሎጂዎችም የተቋሙን ስራ እያቀላጠፉ ነው ብለዋል።
ወንዝ ዳርቻን ጨምሮ የከተማዋን ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡና ከደንብ ጥሰት የጸዱ እንዲሆኑም የቴክኖሎጂ ስራዎች እየሰፉ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።
በፍቃዱ መለሰ