ኢትዮጵያ በቀጣይ አመት ከሶላር ኢንዱስትሪ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ በቀጣይ አመት ከሶላር ኢንዱስትሪ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

AMN-መጋቢት 16/2018 ዓ.ም

በ2019 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከሶላር ኢንዱስትሪ ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከቃና ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያን ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ለማድረግ በርካታ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መንግስት በሶላር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከቬትናም ባስመጣቸው ኢንቨስተሮች አምስት እጅግ ዘመናዊ የሶላር ሴል ማምረቻ ኢትዮጵያ ውስጥ መገንባታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጻ ከፊሎቹ ስራ ጀምረው ኤክስፖርት እያደረጉ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በ2019 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከሶላር ሴል ወጪ ንግድ ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ተናግረዋል።

ይህም በአጠቃላይ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከነበረበት በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ እና ኢትዮጵያ ወደ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ማምረት መሸጋገሯን ትልቅ ማሳያ መሆኑን ነው የገለፁት።

እንዲሁም የኮሪደር እና የቤት ልማት እየተስፋፋ በመሆኑ ግራናይት፣ ማርብል፣ ሴራሚክ፣ መስታወት፣ ብረት እና ሌሎች ግብአቶች በበቂ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከስድስት ወር በኋላ ኢትዮጵያ 100 በመቶ ሴራሚክ ከውጭ እንደማታስገባ የተናገሩ ሲሆን የኢትዮጵያን ፍላጎት ከመሸፈን በላይ የሆኑ ፋብሪካዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ መስታውት ከአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ በኋላ 100 በመቶ በሀገር ውስጥ እናመርታለን ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሁሉም ሴክተሮች በአስደናቂ ሁኔታ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቅርቡ በሞጆ የተጀመረው ነጻ የንግድ ቀጠና ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳቡንም ገልጸዋል።

የአንድ መስኮት እና የዲጂታል አገልግሎት ስለሚሰጥ በርካታ ኢንቬስተሮች በኢንዱስትሪ ፓርክ እና በነጻ የንግድ ቀጠናዎች ላይ እየመጡ ቢሆንም አሁንም በርካታ ስራዎች ያስፈልጉናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሬትና ኢነርጂን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን እየፈታን ሀገሪቱን ለኢንቨስተሮች ምቹ እያደረግን ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በተሟላ መንገድ ኢንዱስትሪው አመርቂ ውጤት እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review