AMN- መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
የአሜሪካ የሰላም ጥያቄ በፓኪስታን በኩል ለኢራን የቀረበ ሲሆን፣ ጦርነቱን ለማርገብ የሚደረገውን ድርድር ፓኪስታን ወይም ቱርክየ ሊያስተናግዱት እንደሚችሉ እየተነገረ ነው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ባለው አስከፊ ጦርነት ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ በዚህም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 15 ነጥቦችን የያዘ የሰላም እቅድ ለኢራን ማቅረባቸው ተሰምቷል። ፓኪስታን እና ቱርክየ ድርድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፣ ቱርክየ በመልእክት ልውውጡ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጻለች።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት የሰላም እቅድ ይዘትም፣ ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን እንድታስወግድ፣ የሚሳኤል መርሐ ግብሯን እንድታቆም እና ለቀጣናው ታጣቂዎች የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቋርጥ የሚጠይቅ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ ኢራን በይፋ ምንም አይነት ድርድር የለም ስትል ያስተባበለች ሲሆን፣ የጦር ቃል አቀባዩ ኢብራሂም ዞልፋቃሪ ትራምፕን፣ “እንደ እኛ ያሉ ሰዎች እንደ እናንተ ካሉ ጋር መቼም አይስማሙም አሁንም ሆነ ወደፊት ከእናንተ ጋር ስምምነት አንፈጽምም ማለታቸው ተገልጿል።

ይህ የሰላም ጭላንጭል መታየቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ በመሬት ላይ ግን ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የአየር ወለድ ወታደሮችን ወደ ባህረ ሰላጤው ለመላክ እያቀደች ነው።
እስራኤል በበኩሏ፣ “ሥራችን እንደተለመደው ነው” በማለት በኢራን ላይ የምታደርገውን ጥቃት ቀጥላለች። ኢራን ደግሞ በቴል አቪቭ፣ በኩዌት እና በባህሬን በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ አዲስ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች።
በታምራት ቢሻው