AMN- መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
በተስፈኝነት እና በእምነት ተሰማሩ የበለጸገች ኢትዮጵያን ትረከባላችሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለቀጣዩ ትውልድ ያማረች፣ የሰመረች እና ከበፊቱ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ እንደሚሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ውብ፣ ጥንታዊት እና ታላቅ ሀገር ናት ሲሉ ገልጸዋታል። ኢትዮጵያውያን ተቀባይ ብቻ ሳንሆን ለዓለም የራሳችንን አስተዎጽኦ ማድረግ የሚያስችል ብቃት እና አቅም ያለን ህዝቦች ነን ብለዋል።
ይህን በ10 ወይንም በ15 ዓመታት አርቀን እያየን እና እያሰብን በትብብር ከገነባን ለብዙዎች ብርቅ፤ መጠለያ መሸሸጊያ የምትሆን ሀገር ትሆናለች ነው ያሉት። ዛሬ ከ1.3 ሚሊየን ያላነሰ ስደተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለ400 ሺህ ኤርትራውያን ቤት የሆነች ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቃና ቴቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሀገራችንን በወግ እና በስርዓት መገንባት ከቻልን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አርአያ መሆን የምትችል፣ የምትተርፍ አድርጎ መሥራት ይቻላል ብለዋል።
ልጆቻችንን እያሰብን የማንገነባት ሀገር እና ከተማ ብዙ እርቀት አትጓዝምና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊ አቅማችን ለትውልድ አስቻይ እና አስተማማኝ የሆነ መሰረት ጥለን እናልፋለን ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ በ10 እና በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አፍሪካ ውስጥ ስመ ጥር ሀገር እንድትሆን አስቻይ መሠረት ከጣልን በኋላ ለ100 ዓመታት የሚዘልቅ ብልጽግና ሊያረጋግጥ እንደሚችል ብሎም ከዚች ሀገር ወጥቶ አፍሪካን ሊያዳርስ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ድንቅ፣ ታሪካዊ፣ ሀብታም መሆንዋን በንግግር ሳይሆን በተግባር ገልጸን የምናሳይበት ወቅት አሁን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትላልቅ ግድቦች፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ በጣም አስደማሚ ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል።
በትዝታ መንግስቱ