አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ አመራሩ እና የመዲናዋ ነዋሪዎች ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ አመራሩ እና የመዲናዋ ነዋሪዎች ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- መጋቢት 16/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ከአመራሩ ጀምሮ፤ የመዲናዋ ነዋሪዎች እና በየደረጃዉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ትልቅ ዋጋ መክፈላቸዉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመትና የኮሪደር ልማት በተሰኙ ጉዳዮች ላይ ከቃና ቲቪ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪደር ልማቱ የተሰራበትን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ የኮሪደር ልማት የሚመች ስራ እንዳልነበረ አንስተዋል፡፡

“ከስራ መልስ ማረፍ ሲገባኝ በምሽት የኮሪደር ልማቱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋዉሬ ለመመልከት እገደዳለሁ“ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”ስራዉ የሚመች ባይሆንም ከተማዋን ለመቀየር እና ለዉጥ ለማምጣት በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ስንሰራ ነበረ“ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በየደረጃዉ የሚገኙ አመራሮች፤ ኮንትራክተሮች እና ሌሎች የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች መዲናዋን ለመቀየር ሌት ከቀን ሲተጉ እንደነበረ እና ትልቅ ዋጋ መክፈላቸዉንም ጨምረዉ ተናግረዋል፡፡

ለልማት ተነሺዎችጋር በተያያዘም ህጋዊ ለሆኑ የልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤት መገንባቱን፤ የንግድ ሱቅ መሰጠቱን እና ሌሎች የስራ ቦታዎች መመቻቸታቸዉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልፎ አልፎ ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘ ተገቢዉን ምላሽ ያላገኙ ቅሬታዎች ካሉ እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ዋና አላማ ነዋሪዎችን ማፈናቀልና መጉዳት አይደለም፤ በፕላን የምትመራ ፤ ያማረች እና ቀጣይ ልማቷ የተረጋገጠ ከተማ መፍጠር ነዉ፡፡

ይህንን አላማ ለማሳካት ብዙዎች ሌት ከቀን ያለ እረፍት ሰርተዋል፤ገንዘብ ያላቸዉ ገንዘባቸዉን ሰጥተዋል፤ ለልማቱ ሲባል የሚነሱ ዜጎችም ከነበሩበት አካባቢ እንዲነሱ ተደርጓል ነዉ ያሉት፡፡ ምንም ዋጋ ሳይከፈል አንድን ከተማ ማልማትም ሆነ ሃገር መገንባት አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባን ጽዱ፤ ዉብ እና አበባ ለማድረግ ትልቅ ዋጋ ተከፍሏል፡፡

በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን አስመልክቶ ተገቢ ያልሆኑ ትችቶችን የሚያነሱ ሰዎች ልማቱንና ለዉጡን ያላዩ ናቸዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ግለሰቦች የተገኙትን ለዉጦች ከማድነቅ ይልቅ በተለያዩ አካባቢዎች ሆነዉ ስለ ሃገሪቱ ሰላምና ልማት አሉታዊ መረጃዎችን ይናገራሉ ብለዋል፡፡

በሃገሪቱ እየተመዘገቡ ያሉትን ልማቶች እና ለዉጦች የሚያጣጥሉት ግለሰቦች በሂደት ይቀርታ መጠየቃቸዉ አይቀርም፤ ኢትዮጵያም ማደጓ፤ በመልጸጓ እና መጽናቷ አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የጀመርነዉ መንገድ እና እሳቤአችን ግልጽ ነዉ ፤ ብዙ ወዳጆችንና ልምድ አግኝተናል፤ ትላንት ከነበረዉ በብዙ እጥፍ እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልማቱን እና ለዉጡን ያልተቀበሉትም በሂደት ይገባቸዋል ነዉ ያሉት፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስት በሚያከናዉናቸዉ የልማት ስራዎች ዙሪያ ስለሚነገሩ አሉባልታዎች ጊዜ የለውም፤ አላማችን የተቀየረችዉን እና የበለጸገችዉን ኢትዮጵያ ማሳየት ብቻ ነዉ ብለዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review