AMN- መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
ወጣቶች ለዛሬውም ሆነ ለነገው የአህጉሪቱ ብልጽግና የማይተኩ አጋሮች ናቸው ሲሉ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ከአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተውጣጡ ወጣቶች፣ ዲፕሎማቶች እና ፖሊሲ አውጪዎች የተሳተፉበት 6ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የዲፕሎማሲ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
“ከፖሊሲ ወደ ትግበራ ለቀጠናዊ ሰላም እና መረጋጋት አፍሪካዊ መፍትሔዎችን በአፍሪካውያን መሪነት ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ፣ ወጣቶች በአህጉሪቱ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጓል።
የጉባኤው ዋና ዓላማ ወጣቶች በአህጉራዊ የሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚ ውህደትና በፈጠራ ሥራዎች ላይ ያላቸውን ሚና ወደ ላቀ ተግባራዊ ደረጃ ማሸጋገር እንደሆነ ተገልጿል።
በመድረኩ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ወጣቶች ለዛሬውም ሆነ ለነገው የአህጉሪቱ ብልጽግና የማይተኩ አጋሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም አፍሪካ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተወዳዳሪ እንድትሆን የዲጂታል ፈጠራ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አጀንዳ 2063ትም ይሁን ሌሎች የዘላቂ የልማት ግቦች የወጣቶች ጉልበት እና ራዕይ ከሌለበት ስኬታማ ሊሆኑ አይችሉም ያሉት ሚኒስትሯ፣ ወጣቶች የቀደሙ ትውልዶችን ጥበብ በመጠቀም የምንመኛት አፍሪካን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሄቨን እያዩ