ጤናማ እና ንቁ ሕይወት እንዲኖርዎት ይፈልጋሉ?

You are currently viewing ጤናማ እና ንቁ ሕይወት እንዲኖርዎት ይፈልጋሉ?
  • Post category:ጤና

AMN- መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

ጤናማ እና ንቁ ሕይወትን በርካቶች ይመኙታል፤ ይህንን ምኞት ለማሳከት በየዕለቱ ትናንሽ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

በየዕለቱ የሚደረጉ ተግባራት በጤና ላይ ትልቅ ውጤት ይኖራቸዋል። ለመሆኑ ለተሻለ ጤና እና ንቁ ህይወት የሚረዱ ዋና ዋና ተግባራት እና ውሳኔዎች ምንድናቸው?

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሰውነታችን በአብዛኛው ከውሃ የተገነባ በመሆኑ በቂ ውሃ መጠጣት ለሁሉም የሰውነት ክፍሎች ሥራ ወሳኝ ነው።

የምግብ መፈጨትን ያፋጥናል፣ ለቆዳ ጥራት ይረዳል፣ እና የሰውነት ድካምን ይቀንሳል፤ በቀን ቢያንስ ከ 8 እስከ 10 ብርጭቆ ውሃ ለመጠጣት መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡

ምግብህን መድሃኒት ካላደረክ መድሃኒትህን ምግብ ታደርገዋለህ የሚል አባባል አለ፤ ምግብ ለሰው ልጅ መድሃኒት ነው፡፡

በቫይታሚንና ሚነራል የበለፀጉ ስለሆኑ አትክልትና ፍራፍሬ በየቀኑ ይመገቡ፤ ለልብ ጤና እና ለደም ግፊት መረጋጋት የስኳርና ጨው መመጠንን መቀነስ ይልመዱ።

ሰውነት መንቀሳቀስ ይፈልጋል ለዚህ ደግሞ የግድ ጂም መሄድ አይጠበቅብዎትም፤ በቀን ለ 30 ደቂቃ በፍጥነት መራመድ የልብ ህመም እና የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ለጤናማና ንቁ ሕይወት ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ጉዳዮች ሌላኛው በቂ እንቅልፍ ማግኘት ነው፡፡

አዕምሯችን እና አካላችን እራሳቸውን የሚያድሱት በእንቅልፍ ወቅት ሲሆን፣ በቀን ከ 7 እስከ 8 ሰዓት መተኛት ለትኩረት፣ ለደስተኛነት እና ለሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ወሳኝ ነው።

አካላዊ ጤና ያለ አእምሮ ጤና ሙሉ አይሆንም ጭንቀትን መቀነስ፦ በጥልቅ መተንፈስ፣ መጽሐፍ ማንበብ ወይም ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ የአእምሮ ሰላምን ይሰጣል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ማንኛውም አይነት የህመም ስሜት ሲሰማዎት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የባለሙያ ምክር ማግኘትም ተገቢ ነው።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review