AMN መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን መካከል እየተካሄደ ባለዉ ጦርነት ምክንያት ሳይካሄድ የቆየዉን ታሪካዊዉን የቻይና ጉብኝት በግንቦት ወር እንደሚያካሄዱ አስታውቀዋል።
ይህ ጉብኝት ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ወደ ቻይና ሲጓዝ የመጀመሪያው ጉዞ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በእቅዱ መሠረት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ጋር በቤጂንግ የሚገናኙ ሲሆን፣ በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ሺን ጂንፒንግን በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚያስተናግዱ በ”ትሩዝ ሶሻል” ማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
ለመጋቢት ወር ታቅዶ የነበረው ጉብኝት የተራዘመው፣ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸሙት መጠነ ሰፊ ጥቃት እና የኢራኑ የበላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ኢራን ለጥቃቱ በሰጠችው ምላሽ በባህረ ሰላጤው አገራት ላይ ጥቃት የሰነዘረች ሲሆን፣ ለአለም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ወሳኝ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።
የመካከለኛዉ ምስራቅ ጦርነት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስንም አስከትሏል።
የነጩ ቤተመንግስት የፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሌቪት እንደገለጹት፣ ፕሬዝዳንት ሺ አሜሪካ አሁን ባለችበት የመካከለኛዉ ጦርነት ምክንያት ትራምፕ በአገራቸው መቆየት እንዳለባቸው ተረድተው የጉዞውን መራዘም ተቀብለዋል።
ቻይና እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ምላሽ ባትሰጥም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ የቴክኖሎጂ እና የጂኦፖለቲካ ውጥረት ያረግባል ተብሎ ይጠበቃል።
በወንድማገኝ አሰፋ