AMN – መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፤ በአዲስ አበባ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የንግድ ሥነ-ምህዳር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገሩን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የንግድ ሥራዎች ቀንሰዋል በሚል የሚሰነዘሩ መከራከሪያዎችን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ልማቱ እጅግ በርካታና ዘመናዊ ሱቆች እንዲሁም የንግድ ማዕከላት እንዲገነቡ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሪ ዐቢይ(ዶ/ር ) በማብራሪያቸው አንድን ትልቅ ራዕይ ለማሳካት ሲባል የሚታጡ ነገሮች መኖራቸው ተፈጥሯዊ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት የያዘው ግልጽ ራዕይ በፕላን የሚመራና ለነዋሪዎቿ የምትመች ዘላቂ ከተማ መፍጠር መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ከፒያሳ እስከ ሽሮ ሜዳ ባለው መስመር ቀድሞ ከነበሩት ሱቆች በተለየ መልኩ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ አካባቢ ለነጋዴዎች ዘመናዊ ሱቆች መገንባታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡባቸው የእሁድ ገበያ አማራጮችና ግዙፍ የገበያ ማዕከላት መመቻቸታቸውን አብራርተዋል።

ይህ አዲስ አሠራር ቀድሞ የነበረውን የደላላ ጣልቃ ገብነት የሚያስቀር ከመሆኑም ባለፈ፣ አምራቾችና አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡና ሸማቹ ማኅበረሰብም ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኝ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አስገንዝበዋል።
ልማቱ ሲከናወን ለተነሱ ዜጎችም መንግሥት ተገቢውን ትኩረት መስጠቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቤት ለሌላቸው ሕጋዊ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት እንዲሁም ሱቅ ለሌላቸው የንግድ ቦታዎች የተመቻቸላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማቱ ቀድሞ የነበረውንና ምቾት የማይሰጥ የከተማ ገጽታ የቀየረ መሆኑን በመጠቆም፣ ለዚህ ስኬት መሃንዲሶች፣ ኮንትራክተሮችና አመራሮች ቀንና ሌሊት መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሚገኙ አክለዋል።
በበረከት ጌታቸው